ከእስር ቤት ሆኖ በምርጫ ላይ ጣልቃ መግባት?

በእስር ላይ ያለው የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ቻርለስ ቴይለር Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በእስር ላይ ያለው የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ቻርለስ ቴይለር

የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ቻርለስ ቴይለር በፈፀሙት የጦር ወንጀል ምክንያት የ50 ዓመት እስር ተፈርዶባቸው በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝ እስር ቤት ውስጥ ነው ያሉት። መቀመጫቸው እስር ቤት ቢሆንም የፊታችን ማክሰኞ በሚደረገው ምርጫ ላይ ጣልቃ ለመግባት እየሞከሩ ይሆን?

እግር ኳስና ፖለቲካ

የቀድሞው ዓለም አቀፍ ታዋቂ እግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ ለሦስተኛ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት እየተወዳደረ ሲሆን፤ በምክትልነትም የቻርለስ ቴይለር የቀድሞ ባለቤት ጂውል ሃዋርድ ቴይለርን መርጦ ለምርጫ ቀርቧል። ጆርጅ ዊሃ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ቻርለስ ቴይለርን እንዲሁም በወቅቱ ሃገሪቷን ይመራ የነበረውን የናሺናል ፓትሪዮቲክ ፓርቲን ለዘመናት ከመተቸቱ አንፃር የአሁኑን ጥምረት ጥያቄ የከተቱ ባሻገር ከጀርባው ሌላ አላማም ሊኖረው ይችላል የሚሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው።

የጆርጅ ዊሃ ፓርቲ የሆነው ኮንግረስ ፎር ዲሞክራቲክ ቼንጅ እና የናሺናል ፓትሪዮቲክ ፓርቲ መጣመር የተሰማው የቀድሞው የጦር አበጋዝ ቴይለር በከፍተኛ ጥበቃ ስር ካሉበት ከእንግሊዝ እስር ቤት ከመደወላቸው በፊት ነው። የስልክ መልዕክቱም አምና በጥር ወር ልደታቸውን ለማክበር ለተሰባሰቡ ደጋፊዎችም ተላልፏል።

"አብዮቱ ህይወቴ ነው" ሲሉ ቻርለስ ቴይለር የተሰሙ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪም ህዝቡ ፓርቲውን እንዳይክድም ሲመክሩ ይደመጣሉ "ወደ መነሻው ተመለሱ ሁሉ ነገርም ጥሩ ይሆናል " ብለዋል።

Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ ጆርጅ ዊሃና ጂውል ሃዋርድ ቴይለር

"እመለሳለሁ"

ጂውል ሃዋርድ ቴይለር ለቀድሞ ባለቤታቸው ታማኝነታቸውን ግልፅ አድርገዋል።

በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ወቅት ለአገሪቷ ጋዜጠኞች በሰጡት ቃለ-መጠይቅ ሃገሪቷን ቻርለስ ቴይለር ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ወዳወጡት "አጀንዳ" ልንመለስም ይገባል ብለዋል።

ነገር ግን በአሁኑ ዓመት በሚደረገውን ምርጫ ላይ ቻርለስ ቴይለር ተፅእኖ እያሳደሩ ነው የሚባለውን አስተባብለዋል። ከዋናዋ ከተማ ሞንሮቪያ ወጣ ብሎ የወዳጅነት ጨዋታ ካደረገ በኋላ ከቢቢሲ ጋር ቀይታ ያደረገው ጆርጅ ዊሃ፤ ቻርለስ ቴይለር ስልክ እንደደወለለት አልካደም።

ቢሆንም ግን በምርጫው የቻርለስ ቴይለር እጅ አለበት የሚለውን አባባል ፈፅሞ አልተቀበለውም። የቀድሞ ባለቤቱን ምክትል አድርጎ ከመምረጡ ጋር ተያይዞም "ሰዎች ይወዷታል፤ የአገሪቷም እናት ነበረች" ብሏል።

በተጨማሪም "ቻርለስ ቴይለር ምርጫውን የሚመራልኝ ቢሆን፤ ዓለም ያውቀው ነበር" በማለትም ይናገራል።

የስልኩ መልዕክት ከተሰማ በኋላ የተለያዩ አካላት እንዳሳሰባቸውም ተናግረዋል። የአሜሪካ ኮንግረስ ማንኛውም ጣልቃ ገብነት በተለይም የጦር ወንጀለኛ ተብለው ከተወነጀሉ ግለሰብ በኩል የሚደረግ ጣልቃ ገብነትን በማውገዝ ውሳኔ አስተላልፏል።

በላይቤሪያ የአውሮፓ ህብረት መልዕክተኛም የትኛውም የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት፤ የተሰጠውን የፍርድ ውሳኔ ገልብጦ ቻርለስ ቴይለርን ወደ ላይቤሪያ መመለስ አይችልም የሚል መግለጫ አውጥቷል።

ፍሮንት ፔጅ አፍሪካ የሚባለው የላይቤሪያ ጋዜጣ አዘጋጅ ሩድኒ ሲህ ለቢቢሲ እንደተናገረውም፤ የቻርለስ ቴይለር ቅርብ የነበሩ ሰዎች በጆርጅ ዊሃ አካባቢ አሉ።

"ምንም እንኳን ቻርለስ በአካል ባይኖሩም አሁን ከቀረቡት ሰዎች ግን አንዳቸው የሚመረጡ ከሆነ በብዙ ነገሮች ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ይቻላሉ" በማለት ተናግሯል።

ተያያዥ ርዕሶች