የቼ ጉቬራ ሃምሳኛ ሙት ዓመት ሲታወስ

Many in Cuba think of Che Guevara as nothing less than a hero Image copyright AFP

የኩባዋ ሳንታ ክላራ ከተማ ዕለተ-እሁድ የቼ ጉቬራ ሙት ዓመትን ለመዘከር በተሰባሰቡ በሺህ በሚቆጠሩ ኩባውያን እና የቼ አድናቂዎች ተጨናንቃ ነበር የዋለችው።

ቼ በፈረንጆቹ ጥቅምት 9/1967 ዓ.ም. ነበር ቦሊቪያ ውስጥ ሕይወቱ የጠፋው።

የቼ የልብ ወዳጅ የነበሩት የአሁኑ የኩባ ፕሬዝዳንት ራውል ካስትሮ በዓሉን ሊያከብሩ ከተሰበሰቡ ሰዎች መካከል ነበሩ።

ብዙዎች በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ፕሬዝዳንት ራወል የቼ መታሰቢያ ሃውልት ላይ ነጭ አበባ ሲያስቀምጡ መመልከት ችለዋል።

ለአምስት አሥር ዓመታት የቼ ምስል ከኩባ የመገበያያ ገንዘብ ጀምሮ እስከ ካናቴራ ድረስ መላ ኩባንና ላቲን አሜሪካን ሲያዳርስ ቆይቷል።

ከላቲን አሜሪካ አልፎም ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላ ዓለም ቼ የነፃነት አርማ ተደርጎ ይቆጠራል። 'ፋኖ ተሠማራ እንደ ሆ ቺ ሚን እንደ ቼ ጉቬራ' የተሰኘውን ስንኝም ከቀደመው ጊዜ ማስታወስ ይቻላል።

በሳንታ ክላራ የተሳበሰቡ ኩባውያን እንደራሳቸው ሰው የሚቆጥሩትን የአርጀንቲናዊው ቼ ጉቬራን ምስል በካናቴራ እንዲሁም በፎቶ በማውለብለብ ሲያስቡት ውለዋል።

"ቼ ለእኛ ኩባውያን ምን ማለት እንደሆነ እናውቃለን። ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለላቲን አሜሪካውያን እና ለዓለም ብዙ አድርጓል። ለዚህም ነው ምስሉን በደረታችን እርሱን ደሞ በልባችን ይዘን የምንዞረው" በማለት አንድ ኩባዊ ይናገራል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ቼ ጉቬራ (ግራ) እና ፊደል ካስትሮ (ቀኝ) ለአራት ዓመታት የኩባን አብዮት መርተዋል።

በፈረንጆቹ 1967 ቼ ሲሞት ሟቹ የኩባ ፕሬዚደንት ፊደል ካስትሮ ያሰሙት ንግግር፤ በተለይ ደግሞ "ኩባውያን ሕፃናት እንደ ቼ ሁኑ" በማለት ያስተላለፉት መልዕክት እንደገና ሲሰማ ውሏል።

በዝክሩ ላይ የተገኙትን ታዳጊ ተማሪዎች ቁጥር ከግምት ውስጥ በማስገባት የቼ ሌጋሲ በኩባ ለሚመጡት በርካታ አስርት ዓመታት ሰርጾ ሊቆይ እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

ደጋፊዎቹ እንደ ቆራጥ ጀግና እና መስዋዕት የሚመለከቱት ቼ በነቃፊዎቹ እንደ ጨካኝ አረመኔ መቆጠሩ አልቀረም።

ሆነም ቀረ ቼ ጉቬራ አሁንም እያከተመ ያለው የኩባ የ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ትውልድ ትልቅ አካል መሆኑ እሙን ነው።

ባለፈው ዓመት ፊደል ካስትሮ ሕይወታቸው ሲያልፍ ለቀብራቸው የወጡ የእሳቸውና የቼ ደጋፊ ኩባውያን አብዛኛዎቹ ዕድሜያቸው በ80ዎቹ የሚገኝ እንደሆነ ተስተውሏል።

ራውል ካስትሮም በሚቀጥለው ዓመት ሥልጣናቸውን ይለቃሉ።

በኩባም ለመጀመሪያ ጊዜ ከካስትሮ ቤተሰብ ውጭ የሆነ ሰው ከ60 ዓመታት በኋላ ወደ ስልጣን እንደሚመጣ ይጠበቃል።

ተያያዥ ርዕሶች