በካሊፎርኒያ ግዛት የተነሳው ሰደድ እሣት ሕይወት እና ንብረት እያጠፋ ነው

At least fourteen fires are burning across eight Californian counties Image copyright Getty Images

ቢያንስ 1500 ቤቶች ወድመዋል። በካሊፎርኒያዋ ሶኖማ በተባለ አካባቢ ደግሞ ሰባት ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን የግዛቲቱ ባለስልጣናት አሳውቀዋል።

በካሊፎርኒያ ታሪክ እጅግ አስከፊው በተባለለት የሰደድ እሣት ምክንያት 20ሺህ ሰዎች ከናፓ፣ ሶኖማ እንዲሁም ዩባ አካባቢዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ሸሽተዋል።

የካሊፎርንያ አስተዳዳሪም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።

"እሣቱ ቤት ንብረት ላይ እያደረሰ ያለው አደጋ እጅግ ከፍተኛ ስለሆነ ሰዎችን ወደሌላ ቦታ ማሸሽ ግድ ይላል" ሲል አዋጁ ያትታል።

በሰደድ እሳቱ ምክንያት ብዙ አደጋዎች እንደተመዘገቡና የተወሰኑ ሰዎች አሁንም ያሉበት እንደማይታወቅ ተዘግቧል።

የካሊፎርኒያ እሣት አደጋ መከላከል ክፍል ኀላፊ እንደተናገሩት ወደ 1500 ቤቶች በሰደዱ ምክንያት ወድመዋል።

እሣቱ ዕለተ-እሁድ ማታ በምን ምክንያት ሊነሳ እንደቻለ አሁንም ማወቅ አልተቻለም።

ናፓ በተሰኘችው አካባቢ የእሣት አደጋ ሰራተኞች ሥራቸውን መከወን ባለመቻላቸው ከፌደራል መንግሥት እርዳታ እንሚያሻቸው የአካባቢዋ አስተዳዳሪ አስታውቀዋል።

በወይን ፋብሪካ ይሰሩ የነበሩ በአስራዎቹ የሚቆጠሩ ሰዎች በተደረገ ርብርብ ከአደጋው መትረፍ መቻላቸውም ተዘግቧል።

Image copyright AFP

የአየር ሁኔታው እና በከፍተኛ ሁኔታ የሚነፍሰው ንፋስ ለሰደዱ መስፋፋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንዳለም ማወቅ ተችሏል።

የአሜሪካ አየር ሁኔታ መሥሪያ ቤት ሰደድ እሣቱ ወደ ሳን ፍራንሲስኮ ግዛትም ሊዛመት እንደሚችል ፍንጭ ስላለ ሰዎች ጥንቃቄ እንዳይለያቸው አሳስቧል።

አንድ የወይን ፋብሪካ ባለቤት ለኤል.ኤ ታይምስ ጋዜጣ ሲናገር "ምንም እንኳ ንብረቴ ቢወድም ቤተሰቦቼን ይዤ ዕሁድ ማታ ማምለጥ ችያለሁ" ብሏል።

የካሊፎርኒያ እሣት አደጋ መስሪያ ቤት እንደሚገምተው ሰደዱ ከ26 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንዳዳረሰ እና በካሊፎርንያ ታሪክ እጅግ አጥፊው እንደሆነ ነው።

ባለፈው ወር የካሊፎርንያዋ ሎስ አንጀለስ በታሪኳ ከፍተኛ የተባለ እሣት አስተናግዳ እንደነበረ የሚታወስ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች