ሰሜን ኮሪያ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ የነደፉትን የጦር ዕቅድ መጥለፏ ታወቀ

North Korean leader Kim Jong-un Image copyright AFP PHOTO/KCNA VIA KNS

የሰሜን ኮሪያ የኮምፒዩተር ጠላፊዎች ከደቡብ ኮሪያ ብዙ ምስጢር እንደያዘ የተነገረለት ወታደራዊ መረጃ ከደቡብ ኮሪያ መጥለፋቸውን እና ከመረጃው መካከል ኪም ጆንግ ኡንን ለመግደል ያለመ ዕቅድ መኖሩም ተረጋግጧል።

ሪ ክሎዊ-ሂ የተባሉ ደቡብ ኮሪያዊ የሕግ ሰው ከደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር መረጃው እንደተገኘ አሳውቀዋል።

መረጃው ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ በጥምረት ሰሜን ኮሪያን ለማጥቃት የወጠኑበት ወታደራዊ ዕቅድ ዝርዝር መረጃ መያዙ ታውቋል።

የሰሜን ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ስለጉዳዩ መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።

ዕቅዱ የደቡብ ኮሪያን አስፈላጊ ወታደራዊ ምስጢሮችን በተለይም ደግሞ የሃገሪቱን ልዩ ሃይል መረጃዎች እንደያዘ ተነግሯል።

ሪ እንደተናገሩት 235 ጊጋባይት መጠን ያለው መረጃ ከደቡብ ኮሪያ መረጃ ቋት ተስርቋል።

ጠለፋው የተካሄደው ባለፈው ዓመት መስከረም ሲሆን በግንቦት ወር ከተሰረቀው መረጃ ጀርባ ሰሜን ኮሪያ ልትኖር እንደምትችል ደቡብ ኮሪያ ፍንጭ ሰጥታ ነበር።

ሰሜን ኮሪያ በጉዳዩ ዙሪያ የምታውቀው ነገር እንደሌለ አሳውቃለች።

የደቡብ ኮሪያው ዮንሃፕ ዜና አግልግሎት ሃገሪቱ የግዙፍ ሳይበር ጥቃት ሰለባ እንደሆነች እና ሰሜን ኮሪያም ለጥቃቱ ተጠያቂ መሆኗን ዘግቧል።

ሰሜን ኮሪያ ለመሰል ተግባራት የሰለጠኑ የኮምፒዩተር ባለሙያዎች እንዳሏት እና የተወሰኑት ቻይና ውስጥ ሆነው እንደሚንቀሳቀሱ እየተነገረ ይገኛል።

Image copyright Reuters

ዜናው መሰማቱ በአሜሪካና ሰሜን ኮሪያ መካከል ያለውን ውጥረት ከማባባስ ውጭ ሌላ ምንም ፋይዳ የለውም ሲሉ ተንታኞች ይገልፃሉ።

ሁለቱ ሃገራት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደተጋጋለ የቃላት ጦርነት የገቡ ሲሆን አሜሪካ ሰሜን ኮሪያ ያላትን ሚሳኤል ማውደም አለባት ስትል ኮሚኒስቷ ሰሜን ኮሪያ ግን ሃሳቡን እንደማትቀበል አስታውቃለች።

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ትራምፕ በቅርቡ በትዊተር ገፃቸው "ዓመታት የፈጀው የቃላት ድርድር ውጤት አልባ ነው። አሁን አንድ ነገር ብቻ ነው የሚሰራው" ሲሉ ዝርዝር የሌለው ጽሁፍ አስፍረዋል።