የካሊፎርኒያ ሰደድ እሣት ማጥፋቱን ቀጥሏል

Santa Rosa in Sonoma County is one of the worst hit area Image copyright Getty Images

ሰደድ እሣቱ በሰሜን ካሊፎርኒያ ባደረሰው ጥፋት እስካሁን 15 ሰዎች መሞታቸው ሲነገር ከ150 በላይ ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም።

አልፎም እሣቱ 1500 ቤቶችን አውድሟል። በቃጠሎው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ሳንታ ሮዛ ከተማ ሙሉ በሙሉ ወደ አመድ ተቀይራለች።

የሶኖማ ከተማ አስተዳዳሪ እንደተናገሩት 150 ሰዎች አሁንም የት እንዳሉ አልታወቀም። ለዚህም ምክንያቱ ከእሣቱ ለማምለጥ የነበረው ግርግር ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል።

በከተማዋ የሚገኘው ሂልተን የተባለው ሆቴል እና ተንቀሳቃሽ ፓርክ ሙሉ በሙሉ መውደማቸውም ታውቋል።

በናፓ ከተማ የ100 እና የ98 ዓመት ባልና ሚስት በሰደዱ ምክንያት ሕይዋታቸው እንደጠፋ ፖሊስ ዘግቧል።

በካሊፎርኒያ ታሪክ እጅግ አስከፊው ከተባለለት ሰደድ እሣት የሚወጣው ጭስ 100 ኪሎ ሜትር ርቃ በትምገኘው ሳን ፍራንሲስኮ ድረስ እየታየ እንደሆነ ማወቅም ተችሏል።

የካሊፎርኒያ እሣት አደጋ መስሪያ ቤት ኃላፊ ኬን ፒምሎት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሰደዱ ከ26 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት አዳርሷል።

• ካሊፎርኒያ እየተቃጠለች ነው

ጨምረውም የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ፍራቻ እንዳላቸው አሳውቀዋል።

"ከከተማዋ በሌላ ምክንያት ወይም እሣቱን ተመልክተው ሸሽተው ሊሆን እንደሚችል ግምታችን ነው። ነገር ግን እሣቱ በፍጥነት እየተዛመተ ስላለ የሚያደርሰው ጥፋት ካሰብነው በላይ ሊሆን ይችላል።"

Image copyright AFP

91ሺህ ያህል ቤቶች ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል ይገኛሉ።

የካሊፎርኒያ ገዥ ሰደዱ ባጠቃቸው ስፍራዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።

ፕሬዝደንት ትራምፕም ከፌዴራል መንግሥት የሚለቀቅ እርዳታ ወደቦታዎቹ እንዲዳረስ አዘዋል።