የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ በላይቤሪያ ምርጫ እየመራ ነው

George Weah is senator for Montserrado County in Liberia Image copyright AFP

የላይቤሪያ ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን በ15 ቦታዎች ከተደረጉ ምርጫዎች በአስራ አንዱ የቀድሞው እግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ እየመራ እንደሆነ ቢያስታውቅም አሸናፊውን ለመለየት ጊዜው ገና እንደሆነ አስታውቋል።

በሌላ በኩል የምርጫው አጠቃላይ ውጤት ይፋ ከመሆኑ በፊት በሃሰት ዜና የተታለሉት የቀድሞው የጆርጅ ዊሃ አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር "የላይቤሪያ ምርጫን ያሸነፈውን ዊሃ እንኳን ደስ አለህ ማለት እወዳለሁ" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የዊሃ ተቀናቃኝ የሆኑት ምክትል ፕሬዚደንቱ ጆሴፍ ቦአካይ በአንድ ምርጫ ጣቢያ እየመሩ ሲሆን በሌሎቹ ጆርጆ ዊሃን በመከተል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በላይቤሪያ ምርጫ አንድ ዕጩ ድሉን ለማወጅ ከ50 በመቶ በላይ ድምፅ ማግኘት አለበት። ይህ ካልተሳካ ሃገሪቱ ኅዳር ወር እንደገና ወደ ምርጫ ትመለሳለች።

የአሁኑ የላይቤሪያ ምርጫ በአፍሪካ የመሪዎች ታሪክ ቀዳሚ ሴት ፕሬዝዳንት የሆኑትን የኖቤል ሽልማት አሸናፊዋን ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍን ለመተካት እየተካሄደ ያለ ነው።

የላይቤሪያ ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን ዤሮም ኮርኮያ በመናፈስ ላይ ያሉ ሃሰተኛ ዜናዎችን ወርፈው "ኮሚሽናችን ትክክለኛውን ውጤት በቅርቡ ይፋ ያደርጋል" ሲሉ አሳውቀዋል።

ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች የላይቤሪያ ምርጫ ላይ ምንም ዓይነት ችግር አልታዘብንም ብለዋል።

ነገር ግን ሮይተርስ የተሰኘው የዜና ወኪል 20 የሚሆኑ ዕጩዎች ምርጫው የተከወነበት ሂደት ፍትሐዊ አይደለም በማለት ጥያቂ ሊያቀርቡ እየተዘጋጁ እንደሆነ አሳውቋል።

ሁለት ጊዜ ላይቤሪያን በፕሬዚደንትነት ያገለገሉት የ78 ዓመቷ ሰርሊፍ ምርጫው እጅግ ስኬታማ ነበር ሲሉ አሳውቀዋል።

"ሁሉም ላይቤሪያውያን ለዚህ ሂደት ዝግጁ እንደሆኑ አምናለሁ። ለዚህም ምስጋናዬን ማቅረብ እወዳለሁ" ብለዋል።

ሰርሊፍ በ2006 (እአአ) ነበር ከቀድሞው ፕሬዝደንት ቻርልስ ቴይለር ስልጣን የተረከቡት።

ቻርልስ ቴይለር በአሁኑ ወቅት በጦር ወንጀል ክስ የተበየነባቸውን የ50 ዓመት እስር በእንግሊዝ በመፈፀም ላይ ናቸው።