በመጨረሻ ዙማ ይከሰሱ ይሆን?

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ዙማ Image copyright Reuters

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ በሙስና፣ በማጭበርበር፣ ገንዘብ በሕገ-ወጥ መንገድ በማዘዋወርና የህዝብን ገንዘብ ያለአግባብ በመጠቀም እንዲከሰሱ ይግባኝ ሰሚ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወሰነ።

ከ17 ዓመት በፊት ከነበረ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነት ጋር በተያያዘ አቃቤ ህግ 783 የሚሆኑ የሙስና ክሶች እንዲቀርቡም ከታችኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ጋር ተስማምቷል።

ይህ ክስ ከስምንት ዓመት በፊት ወደ ጎን ተትቶ ዙማ ፕሬዚዳንት ለመሆን ችለዋል።

ዙማ ንፁህ ነኝ ማለታቸውንም ቀጥለዋል።

ክሱ ከ12 ዓመታት በፊት ለዙማ ጥቅም ሲል ሻቢር ሼክ የተባለ ነጋዴ ከፈረንሳይ የመሳሪያ አምራች ኩባንያ ጉቦ በመቀበል ጥፋተኛ ከሆነበት ድርጊት ጋርም ይገናኛል።

ይህ ክስ በጊዜው ዙማም ላይ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም ከስምንት ዓመት በፊት ውድቅ ተደርጓል።

ዙማም ሆኑ ሌሎች የመንግሥት ባለስልጣናት ከተዋጊ ጀቶች፣ ጀልባዎች እንዲሁም ከጦር መሳሪያ ግዢዎች ጋር በተያያዘ ገንዘብ ወስደዋልም ተብለው ይወነጀላሉ።

ዲሞክራቲክ አሊያንስ ፓርቲ ባለፈው ዓመት እንደገና ክስ የመሰረተ ሲሆን ፕሪቶሪያ የሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ክሱን ተቀብሏል።

የፕሬዚዳንቱ የህግ አማካሪዎች ውሳኔውን "ያልበሰለ አካሄድ" ብለውታል።

የስለላ የስልክ ንግግሮች

ይህ የሙስና ክስ በቀላሉ እንደማያበቃ እየተነገረ ነው።

ፕሬዚዳንት ዙማ በ783 የሙስና ክሶች ወደ ፍርድ ቤት እንዳይሄዱ ብዙ ታግላዋል።

ከዓመታት በፊት አነጋጋሪ በሆነ ሁኔታ ክሱ ውድቅ የተደረገው፤ የደህንነት ሰዎች የአቃቤ ህጎችን የስልክ ንግግር ጠልፈው በማሰማት "ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት" ታይቶበታል በሚል ነበር።

ይህንን ተከትሎም ዙማ ከሳምንታት በኋላ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት በመሆን አሸነፉ።

ይህ የስልክ ንግግር በአደባባይ ያልተገለጠ ሲሆን፤ ተቃዋሚዎቻቸው የሙስናው ክሱ ተመልሶ እንዲንቀሳቀስ ብዙ ታግለዋል።

ፍርድ ቤቱ በፅንሰ-ሃሳብ ደረጃ ይግባኙን ቢቀበለውም በተግባር ግን አቃቤ ህግ ክሱን ያጓትተዋል የሚሉም አልታጡም።

የዙማ የአመራር ጊዜ ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚያበቃ ሲሆን ለሶስተኛ ዙር መመረጥ አይችሉም።

ከአፓርታይድ ሥርዓት መወገድ በኋላ በደቡብ አፍሪካ ወደ ሥልጣን ከመጡ አነጋጋሪ አመራሮች ቀዳሚ የሆኑት ዙማ፤ ለዓመታት በፓርላማው ስምንት ያህል ጊዜ የመተማመኛ ድምፅ ቢሰጥባቸውም በመንበራቸው ላይ ለመቆየት ችለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች