ህመሙ እየከፋ የሚገኘው ዓባይ፡ ከጣና ሃይቅ እስከ ታላቁ ህዳሴ ግድብ

ዓባይ
አጭር የምስል መግለጫ እየተመናመነ የመጣውን ውሃ ለመጠቀም የሚደረገው ፉክክር በአካባቢው ሃገራት መካከል ግጭት ሊፈጥር ይችላል

የዓለማችን ረዥሙ ወንዝ ከመታመም በላይ ህመሙ እየከፋ ነው።

ክፍል 2 ፡የህዝብ ብዛት መጨመርና የአካባቢ ብክለት ሌሎቹ የዓባይ ስጋቶች

ክፍል 3 ፡የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ መፃኢ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?

የህዝብ ቁጥር መጨመር ውሃውን እያቆሸሸው እና እያደረቀው ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥ ደግሞ መጠኑን እየቀነሰው ይገኛል።

አንዳንዶች ደግሞ እየተመናመነ የመጣውን ውሃ ለመጠቀም የሚደረገው ፉክክር በአካባቢው ሃገራት መካከል ግጭት ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

በዓባይ ዙሪያ በሦስት ክፍሎች ከምናቀርበው ዘገባ፤ በመጀመሪያው ክፍል ወንዙ ስለገጠመውን ፈተና፣ ስለተፈጥሮ ሃብቱ እና ስለአካባቢው ህዝቦችን ዕጣ ፈንታ እንመለከታለን።

ዝናብ

ችግሩ የሚጀመረው ከወንዙ መነሻ ነው።

የዓባይ ወንዝ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን የውሃ መጠን በኢትዮጵያ ከሚጥለው ዝናብ ያገኛል።

ከጣና ሐይቅ በስተደቡብ ከሚገኘው ጫካ ውስጥ የሚነሳው ጥቁር ዓባይ በመጠኑ እያደገ ይሄዳል።

ከቪክቶሪያ ሃይቅ የሚነሳው ነጭ ዓባይ በበኩሉ አነስተኛ መጠን ያለው ውሃ ይዞ ካርቱም ላይ ከኢትዮጵያው ጥቁር ዓባይ ጋር ይቀላለቀላል።

በኢትዮጵያ ዝናብ እንደዚህ ቀደሙ እየዘነበ አይደለም። ይህ ደግሞ ዓባይ ሙሉ ለሙሉ እንዲሞት ሊያደርገው ይችላል።

ከረዥም የበጋ ወቅት በኋላ በየዓመቱ የሚኖረው አጭር የዝናብ ወቅት አንዳንዴ አነስተኛ ዝናብ ብቻ ይዞ ይመጣል።

"ዝናቡ አሁን ይበልጥ የማይገመት ሆኗል። አንዳንዴ ጠንካራ ሌላ ጊዜ ደግሞ አነስተኛ መጠን ያለው የዝናብ ወቅት ይሆናል። መጠኑ ሁሌም የተለያየ ነው" ይላል የአርባ ምንጭ ዩንቨርሲቲ መምህሩና የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪው ላዕከማርያም ዮሃንስ።

አጭር የምስል መግለጫ የዓባይ ወንዝ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን የውሃ መጠን በኢትዮጵያ ከሚጥለው ዝናብ ያገኛል

ከባድ የሆነ የክረምት ወቅት ሲኖር ወንዙ በቢሊዮን ቶኖች የሚቆጠር ለም አፈርን ከኢትዮጵያ በየዓመቱ ይዞ ይሄዳል። ይህ ደግሞ ግድቦችን የሚገድልና አርሶ አደሮች የሚያስፈልጋቸውን ለም አፈር የሚያሳጣ ነው።

ይህ ችግር በህዝብ ቁጥር በፍጥነት ማደግ ምክንያት ተባብሷል። የቤተሰብ መስፋፋትን ተከትሎ ሰዎች መኖሪያቸውን ለመቀለስ የሚረዳቸውን ቦታ እና ቁሳቁስ ለማግኝት ዛፎችን እየቆረጡ ነው።

ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትሉ ጎርፎችም በተደጋጋሚ መከሰት ጀምረዋል።

የሰብሎች ምርታማነት እየቀነሰ እና የምግብ ዋጋ ደግሞ እየጨመረ ይገኛል። በዚህም ወንዞችን በመስኖ ከመጠቀም ይልቅ ዝናብ ላይ የተመሰረተ ግብርና ላይ የሚተዳደሩ የገጠር መንደሮች ወደ ድህነት እየተሸጋገሩ ይገኛሉ።

አንዳንድ የገጠር ነዋሪዎች የግብርና ሥራቸውን እርግፍ አድርገው በመተው ወደ ክልሉ ርዕሰ መዲና ባህር ዳር ወይንም በማደግ ላይ ወደምትገኘው የአገሪቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ማቅናትን መርጠዋል።

አብዛኛዎቹ ሰዎች ዝናቡ እንደቀድሞው ይሆናል በሚል ተስፋ ያገኙትን ውሃ በመጠቀም ህይወታቸውን ለመግፋት ተገደዋል።

ለአንዳንድ ታዳጊዎች ግን ተስፋ አስቆራጭ ሆኗል።

ቤተሰቦቹን በእርሻ ሥራቸው ለመደገፍ ትምህርቱን አቋርጦ ያለችውን ብስክሌት በመሸጥ አዲስ ምርጥ ዘር የገዛው የ17 ዓመቱ ጌትሽ አዳሙ በስደት ሜድትራኒያንን ስለማቋረጥ እያሰበ ይገኛል።

"ቆም ብዬ ሳስበው ከቤተሰቤ ጋር መኖር እፈልጋለሁ። ነገር ግን ዝናቡ እንዲህ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ እዚህ ስፍራ መቆየት አልችልም" ይላል።

አጭር የምስል መግለጫ አንዳንድ የመንደሩ ነዋሪዎች የግብርና ስራቸውን እርግፍ አድርገው ትተዋል

የግድብ ውዝግብ

ዓባይ ብዙ በተጓዘ ቁጥር ያለበትም ችግር እየጨመረ ይሄዳል።

30 ማይሎችን ያህል ከጣና ሃይቅ ከራቀ በኋላ አስደማሚውን የዓባይ ፋፏቴን አልፎ በጠመዝማዛው ገደላ ገደል ውስጥ ጉዞውን ይቀጥላል።

ገባሮቹን ወንዞች ተጠቅሞ የሚያገኘውን ውሃ እየጨመረ ጉልበቱን እያጠናከረ በመሄድ ከከፍተኛ ቦታ የጀመረውን ጉዞ ወደ ዝቅተኛ አካባቢዎች ያደርጋል። ይህም እጅግ በጣም ቆንጆ፣ የተነጠለ እና ምናልባትም በጣም ያልተረጋጋው የውሃው መንገድ ይሆናል።

አጭር የምስል መግለጫ የህዳሴው ግድብ ሰባት ጌጋ ዋት ኃይል ያመነጫል

በአፍሪካ ትልቁ ከሆነው የኤሌክትሪክ ግድብ ጀምሮ እስከ ወንዙ አቅራቢያ የሚኖሩና መሬቶቻቸው በግብርና ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ትላልቅ የውጭ ባለሃብቶች ተሰጥቶባቸው እስከተፈናቀሉ ሰዎች ድረስ ብዙ ያልጠራ ነገር አለ።

ከስፍራው ሆኖ መዘገብ ማለት የፈሩ ቃለመጠይቅ ሰጪዎችና ውስብስብ የሆኑ የፍተሻ ቦታዎች ያሉት የማዕድን ቦታዎችን እንደመጎብኘት ነው።

"የማንናገራቸው ጉዳዮች እንዳሉ ልትረዳ ይገባል" ይላል በእንጅባራ የምግብ ቤት ባለቤት ሆነው ሳሙኤል። "እነዚህ ጥያቄዎች ችግር ውስጥ ሊከቱህ ይችላሉ" ሲል ያክላል።

ንግግሩ ግነት የለበትም። ከቀናት በኋላ የደህነነት ሃይሎች የሆቴሌን ክፍል ወረው ማስታወሻ መያዣ ደብተሬን ብቻ ወስደዋል።

በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ስለተወረሱ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ለመዘገብ ስጓዝ ቻግኒ አቅራቢያ በሚገኝ የፖሊስ ፍተሻ ጣቢያ ላይ ወደ ኋላ እንድመለስ ተነግሮኛል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

የህዳሴው ግድብ ሰባት ጌጋ ዋት ኃይል የሚያመነጭ እና ለበርካቶች ኩራት ከመሆን ባለፈ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የአሌክትሪክ ኃይል ያስገኛል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል።

ከታችኛው የውሃው ተፋሰስ ሃገራት አንዷ ሆነችው ግብጽ፤ ግድቡ የዓባይን ውሃ ይቀንሳል የሚል ስጋት አላት። አብዛኛው የሃገሪቱ ክፍል በረሃማ ከመሆኑም በላይ በየዓመቱ የሚጥለው ዝናብ ጥቂት በመሆኑ፤ ሃገሪቱ 95 በመቶ የሚሆነውን የውሃ ፍላጎቷን ከዓባይ ታሟላለች።

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ እና ሌሎች የታችኛው የተፋሰሱ ሃገራት ህጋዊነቱን ቢቃወሙትም፤ እ.ኤ.አ በ 1959 የተደረሰው ስምምነት የዓባይን ውሃ ሙሉ ለሙሉ ለግብጽ እና ለሱዳን ሰጥቷል። ይህን ግን አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት በራሳቸው ጉዳይ የነበራቸው ሚና አነስተኛ በነበረበት በቅኝ ግዛት ዘመን ነው የተደረገው በሚል ነው የሚቃወሙት።

አጭር የምስል መግለጫ እ.ኤ.አ በ 1959 የተደረሰው ስምምነት የዓባይን ውሃ ሙሉ ለሙሉ ለግብጽ እና ለሱዳን ሰጥቷል

ከካይሮ የጦርነት ዛቻዎች እየተወረወሩ ሲሆን በሁለቱም በኩል ጠንካራ የቃላት ልውውጦች ነበሩ። ውሃን ምክንያት በማድረግ በአካባቢው ግጭት ቢከሰት፤ ይህ በጣም አስገራሚ ወንዝ ቀዳሚው ምክንያት ሊሆን ይችላል።

"ሠላም ይሆናል? አይሆንም" ይላል ጣና ዳር በሚገኘው ባህር ዳር ተብሎ በሚጠራው ግሮሠሪ ቢራ ስጠጣ ያገኘሁት ሞሰስ የተባለ የባሕር ኃይል መኮንን። "ሁላችንም የጦር ግንባር ላይ እንደሆንን እንረዳለን። ውሃው፣ ግድቡም፣ ምርጡም መሬት እዚሁ ነው" ይላል።

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር እ.አ.አ በ1991 ከተለያየች በኋላ የባህር በር ባይኖራትም ጣና ሐይቅ ላይ ያላትን የባሕር ኃይል ተቋም ጠብቃ አቆይታለች። "ተቋሙ ወደፊት ሊጠቅመን ይችላል" ሲል ሞሰስ ይገልጻል።

ክፍል 2 ፡የህዝብ ብዛት መጨመርና የአካባቢ ብክለት ሌሎቹ የዓባይ ስጋቶች

ክፍል 3 ፡የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ መፃኢ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?

ተጨማሪ ፡ጣና ሐይቅ የተጋረጡበት ፈተናዎች