ሶማሊያ፡ በሞቃዲሾ ፍንዳታ ከ270 በላይ ሰዎች ሞቱ

ሞቃዲሾ ከፍንዳታው በኋላ
አጭር የምስል መግለጫ ሞቃዲሾ ከፍንዳታው በኋላ

በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ቅዳሜ ዕለት በደረሰ ከፍተኛ የሆነ የቦምብ ፍንዳታ ከ270 በላይ የሚሆኑ ሰዎች እንደሞቱ ፖሊስ ተናግሯል።

በጥቃቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቆሰሉ ሲሆን ፍንዳታው የደረሰው በአንድ ሆቴል በር ላይ የቆመ የጭነት መኪና ውስጥ የነበረው ተቀጣጣይ የሆነ ቦምብ በመፈንዳቱ ነው።

የኢስላማዊው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ የስርጎ ገብ ጥቃቱን ካወጀ ከ10 አመት በኋላ ከፍተኛ የሚባል አደጋ ነው።

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ በጥፋቱ አልሻባብን ወንጅለው "ሰይጣናዊ ተግባር ብለውታል። "

ለፍንዳታው ኃላፊነቱን የወሰደ ቡድን የለም።

"ወንድሞች ይህ ጭካኔ የተሞላበት ተግባር የተፈፀመው የየዕለት ተግባራቸውን ሲያከናውኑ በነበሩ ንፁኃን ላይ ነው።"በማለት ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

በፍንዳታው ተጠቂ ለሆኑትም ሶስት የኃዘን ቀናትን አውጀዋል።

የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት እሁድ ቀን ቤተሰቦቻቸው የጠፉባቸው ሰዎች በፈራረሱ ህንፃዎች መካከል ሲፈልጉ ነበር።

ኢብራሂም ሞሐመድ የተባሉ ፖሊስ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የተናገሩት የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ነው። " ከሶስት መቶ በላይ የሚሆኑት ቆስለዋል፤ የአንዳንዶቹም ጉዳት ከፍተኛ ነው። " ብለዋል

በተጨማሪ ሁለተኛ የቦምብ ፍንዳታ በመዲና ከተማ የሁለት ሰዎችን ህይወት እንደቀጠፈም ባለስልጣናቱ ይናገራሉ።

የሞቃዲሾ ከንቲባ ታቢት አብዲ የቦምብ ጥቃቱን ለመቃወም የመጡ ሰልፈኞችን ህብረት እንደሚያስፈልግ አፅንኦት ሰጥተዋል።

"የሞቃዲሾ ህዝብ ሆይ፤ ሞቃዲሾ በእሳት ለተቃጠሉ ሬሳዎች የመቃብር ስፍራ መሆን የለባትም፤ ሞቃዲሾ መከባበር የሰፈነባት ቦታ ናት። ዛሬ በህብረት እንደቆምነው የምንቀጥል ከሆነ ከአምላክ ፈቃድ ጋር ጠላታችንን እናሸንፋለን። "ብለዋል

በቦታው የተገኘው የቢቢሲ ሶማሊ ዘጋቢ እንደገለጸው በፍንዳታው ምክንያት የሳፋሪ ሆቴል ሙሉ በሙሉ የወደመ ሲሆን ብዙዎች በፍርስራሹ ውስጥ ተቀብረው ነበር።

የአካባቢው ነዋሪና የአይን እማኝ ሙህዲን አሊ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገሩት " አካባቢውን የደመሰሰ ትልቅ ፍንዳታ ነው። "ብለዋል።

በተጨማሪ የመዲና ሆስፒታል ዳይሬክተር ሞሃመድ የሱፍ ሀሰን በቦምብ ፍንዳታው እንደተደናገጡ ተናግረዋል።

" በሆስፒታሉ ሰባ ሁለት ሰዎች ቆስለው መጥተዋል፤ ከነዚህ 25ቱ በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። እጃቸውንና እግራቸውን ያጡ ብዙ ናቸው። " ጨምረውም እንደዚህ አይነት አደጋ አጋጥሟቸው እንደማያውቅና ሬሳዎች የማይታወቅ ደረጃ ላይ ደርሰው መቃጠላቸውንም ጭምር ተናግረዋል።

አጭር የምስል መግለጫ በሞቃዲሾ ሰልፈኞች ቦምብ ጥቃቱን በማውገዝ ሲቃወሙ

አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥቃቱን ለማውገዝ ፈጣን ምላሽ ሰጥቷል

  • የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ሙሳ ፋቂ ማሃማት ኮሚሽኑ ዘላቂ የሆነ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ድጋፋቸውን እንደሚለግሱ ተናግረዋል።
  • የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒሰትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለጥቃቱ ሰለባዎች የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
  • ቱርክ መድሃኒቶችና ቁሳቁሶችን በአውሮፕላን ለመላክ ቃል የገባች ሲሆን፤ የቆሰሉ ሰዎችም ቱርክ ሄደው የሚታከሙበትን መንገድ እፈጥራለሁ ብላለች።
  • በሶማሊያ የአሜሪካ መልዕክተኛ በሰጠው መግለጫ ፍንዳታው " የፈሪዎች" ተግባር እንደሆነ ጠቅሶ አሜሪካ ሽብርተኝነትን በመታገል ለአፍሪካውያን የምታደርገውን እርዳታ ያጠናክረዋል ብለዋል።
  • የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው ኃዘናቸውን ጥቃቱ ለደረሰባቸው ቤተሰቦች እንዲሁም በሀሳብ ከሶማሊያ መንግስትና ሕዝብ ጎን መሆናቸውን ተናግረዋል።
  • የተባበሩት መንግስታት ፀሐፊ ጄኔራል አንቶኒዮ ጉተር በትዊተር ገፃቸው "የሚያሳምም ተግባር" ካሉ በኋላ በሽብርተኝነትና በጭፍን ጥላቻ ውስጥ አንድነትን ማሳየት አለብን ብለዋል።
  • የ ፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም በትዊተር ገፃቸው ፈረንሳይ ከሶማሊያ ጎን ትቆማለች ብለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች