የመጀመሪያው ጥቁር የኦክስፎርድ ተማሪ ክሪስትያን ኮል

Christian Cole was depicted in cartoons during his time at Oxford Image copyright BODLEIAN LIBRARY

ኦክስፎርድ የመጀመሪያው ጥቁር ተማሪ ሆኖ በዩኒቨርሲቲው የተመዘገበውን ሴራሊዮናዊ ክሪስትያን ኮልን ሰሞኑን አስታውሷል።

ነገር ግን ክሪስትያን ኮል ማነው? ጥቁር ሆኖ ዩኒቨርሲቲ መቀላቀል 'አስደናቂ' በሚባልበት ወቅት ይህንን እንዴት ማድረግ ቻለ?

የክላሲክ ሙዚቃ ስልትን ሊያጠና ወደ ኦክስፎርድ ብቅ ያለው ጥቁሩ ኮል ቅጥር ግቢውን ሲረግጥ የወሬ ርዕስ መሆኑ አልቀረም።

ጊዜው በአውሮፓውያኑ 1873 ነበር። የ21 ዓመቱ ኮል ከሴራሊዮን ዋተርሉ ከተማ በመምጣት በወቅቱ አቅም ያላቸው እንግሊዛውያን የሚማሩበትን ትምህርት ቤት ተቀላቀለ። ይህም ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪየውን የሴቶች ትምህርት ቤት ከማቋቋሙ ስድስት ዓመታት ቀደም ብሎ ነው።

"ከተማዋ አስፈሪ ነገር ሆና ሳትጠብቀው አትቀርም" ይላሉ የዩኒቨርሲቲው የማሕደር ባለሙያ ዶ/ር ሮቢን ዳርዋል ስሚዝ።

"በዚያን ጊዜ ለነበሩ ተማሪዎች ኮል፤ በሕይወታቸው ያዩት የመጀመሪያው ጥቁር ሠው ሳይሆን አይቀርም" ይላሉ ዶ/ር ሮቢን።

'የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር ተማሪዎች ያልተነገረ ታሪክ' የሚል መጽሓፍ ያሳተሙት ታሪክ አጥኚዋ ፓሜላ ሮበርትስ እንደሚያምኑት፤ ለኮል ከሴራሊዮን ወደ ብሪታኒያ የእንግሊዝኛ አነጋገር ዘይቤውን መቀየር በራሱ ፈታኝ ነገር ነበር።

እርግጥ ኮል ሴራሊዮን እያለ ምን ዓይነት ሕይወት ይመራ እንደነበር ብዙ የሚታወቅ ነገር የለም። ቢሆንም ትምህርት የመቀበል ልዩ ችሎታው ከሌሎች ነጥሮ እንዲወጣ ምክንያት እንደሆነው ፓሜላ ይናገራሉ።

Image copyright UNIVERSITY COLLEGE

ኮል ሴራሊዮን ውስጥ የእንግሊዝ ቤተክርስትያን ቄስ የነበሩ ሠው የማደጎ ልጅ ነበር።

በሴራሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታውን ባለ ታዋቂ ትምህርት ቤትም ተማሪ ነበር። በኦክስፎርድ ቆይታውም የመክፈል አቅም የሌላቸው ተማሪዎች በሚረዱበት ሥርዓት ውስጥ ነበር የተማረው።

ከአጎቱ የሚላክለትን መጠነኛ ገንዘብን በትርፍ ጊዜ የሙዚቃ ትምህርት በማስተማር ከሚያገኘው ጋር አድርጎ ራሱን ይደጉምም ነበር።

እንዲህ ራሱን ለመደጎም ላይ ታች ቢልም በኦክስፎርድ ሕይወቱ ሰኬትን ከማጣጣም አላገደውም ነበር ሲሉ ዶ/ር ሮቢን ይተርካሉ።

በዩኒቨርሲቲው የመከራከሪያ መድረክ ላይ ንግግር ያደርግ የነበረው ሲሆን፤ በኦክስፎርድ የተማሪዎች ሕብረትም የነቃ ተሳትፎ አድርጓል። ታዋቂነትንም አትርፎ እንደነበረም ይወሳል።

በስተመጨረሻም ዩኒቨርሲቲው የክብር ድግሪ በሚሰጥበት ሥነ-ሥርዓት ላይ የክርስቲያን ኮል ስም ሲጠራ የነበረውን ጩኸት እና ጭብጨባ ዩኒቨርሲቲው በታሪክነት አስቀምጦታል።

"ሥነ-ሥርዓቱን ለመታዘብ የመጡ ሠዎች ማነው ይህ እንዲህ የሚጨበጭብለት ሲሉ 'ክሪስትያን ኮል ነው። ከሴራሊዮን ነው የመጣው' ብለው ሲናገሩ ይታሰበኛል" ሲሉ ዶ/ር ሮቢን ያወሳሉ።

ተያያዥ ርዕሶች