በኬንያ የሚገኙ ኦሮሞ ስደተኞች ፖሊስ እገዳ እንዳበዛባቸው ይገልጻሉ

በኬንያ ናይሮቢ በ2008 የተከበረው የኢሬቻ በዓል
የምስሉ መግለጫ,

በኬንያ ናይሮቢ በ2008 የተከበረው የኢሬቻ በዓል

የኬንያ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ መንግሥት ግፊት በሃገራቸው የሚገኙ ስደተኞች ላይ እገዳ እየጣሉባቸው መሆኑን የስደተኞች ቡድንና ሂውማን ራይትስ ዋች ገለጹ።

የኦሮሞ ስደተኞች መስከረም 22/2010 ዓ.ም የኢሬቻ በዓልን በይፋ ለማክበር ያቀረቡት ጥያቄ ውድቅ መሆኑን ተከትሎ ጥቅምት 5/2010 በዓሉን በግል ይዞታ ላይ አክብረዋል።

እነሱ እንደሚሉት ይህ በተከታታይ በኬንያ ባለስልጣናት ከሚጣሉባቸው ገደቦች አንዱ ነው።

ዲሪርሳ ቀጄላ በኬንያ የሚገኘው የኦሮሞ ስደተኞች ማህበር የህዝብ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ነው።

ዲሪርሳ እንደሚለው ችግሩ የጀምረው እ.አ.አ በ2015 በእድሜ ባለጸጋው የባህል እና የታሪክ አዋቂው ዳበሳ ጉዮ የት እንደደረሱ ከጠፉ በኋላ ነው። ግለሰቡ ከናይሮቢ ቤታቸው የጠፉት በዚያ ዓመት ከተካሄደው ኢሬቻ ክብረ በዓል በኋላ ነበር።

በ2016 የተከበረው የኢሬቻ ክብረ በዓል ከመጀመሩ በፊትም 42 ኦሮሞዎች በኬንያ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለዋል። ናይሮቢ ውስጥ ህገወጥ የኦሮሞ ማህበረሰብ ሊያቋቁሙ ነው በሚል ነው የተያዙት።

"የኢትዮጵያ መንግሥትን ሊያስቆጣ ይችላል"

"ባለፉት 15 ዓመታት ኢሬቻን እያከበርን ብንቆይም ዘንድሮ ለማክበር ያቀረብነው 'ህጋዊ ጥያቄ' ውድቅ ተደርጎብናል" ሲል ዲሪርሳ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የዓመታዊውን ክብረ በዓል ዓላማ እና እስከ 200 የሚደርሱ ሰዎች እንደሚሳተፉበት በመጥቀስ በናይሮቢ ሲቲ ፓርክ ለማክበር የጽሑፍ ጥያቄ ቀርበው ነበር።

የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽን ጥያቄውን ለጊጊሪ ፖሊስ ጣቢያ ቢመራውም ጥያቄያቸው ውድቅ መደረጉን ዲሪርሳ አስታውቋል።

ማህበሩ ስለጉዳዩ ናይሮቢ ከሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፈቃድ መጠየቅ እንዳለበት ተገልጾላቸዋል። ፖሊስ ፈቃዱን የሚሰጠው ከኤምባሲው ፈቃድ ከተገኘ በኋላ ነው ተብለዋል።

"የፖሊስ ጣቢያው አዛዥ 'በፖለቲካዊ ምክንያቶች' ኦሮሞዎች እንዲሰበሰቡም ሆነ በዓል እንዲያከብሩ ፈቃድ እንደማይሰጡ ገልጸውልናል። ሆኖም እነዚህ 'ፖለቲካዊ ምክንያቶች' ምን እንደሆኑ ግልጽ አላደረጉልንም" ሲል ዲሪርሳ አስታውቋል።

እንደዲሪርሳ አገላለጽ ከሆነ ኤምባሲውን ሳያማክሩ ክብረ በዓሉ እንዲካሄድ ቢፈቅዱ "የኢትዮጵያ መንግሥትን ሊያስቆጣ ይችላል" ተብለዋል።

የምስሉ መግለጫ,

ዳበሳ ጉዮ በ2008 ኬንያ በተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ

የስደተኖች ጉዳይ

በኬንያ የህዝብ ሥነ-ምግባር ህግ አንቀጽ 56 እንደሰፈረው ከሆነ ለማህበራዊ፣ ባህላዊ እና ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰባሰብ ፈቃድ አያስፈልገውም። በዚህ መሠረት ኢሬቻ እንዳይከበር የሚከለክል ምክንያት አልነበረም።

ኢሬቻ ባህላዊ ክብረ በዓል ቢሆንም ኦሮሞ አክቲቪስቶችን ጨምሮ የተለያዩ ወገኖች ክብረ በዓሉን ፖለቲካዊ ተቃውሞዎች የሚሰሙበት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የማህበሩ አባላት ስደተኞች በመሆናቸው ከኤምባሲው ጋር ግንኙነት መፍጠር አለመቻላቸውን ለቢቢሲ አስታውቀዋል።

"ስደተኞች በመሆናችን ስለጉዳዩ ኤምባሲውን ለመጠየቅ መብት የለንም" ይላል ዲሪብሳ።

ብዙዎቹ ስደተኞች ኢትዮጵያን ለቀው የወጡት በፖለቲካ ምክንያት ነው።

"ደህንነት አይሰማኝም" ይላል። "እታሰራለሁ ወይንም ታፍኜ ወደ ኢትዮጵያ ልመለስ እችላለሁ የሚል ፍራቻ አለኝ። እስከማውቀው ድረስ የኬንያ ፖሊስና ኢትዮጵያ መንግሥስት ይህንን በተደጋጋሚ ሲያደርጉት ቆይተዋል" ብሏል።

"ይህንንም እንደስደተኞች ጉዳይ እና ለተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ላሉ ድርጅቶች በተደጋጋሚ መረጃ ሰጥቻለሁ" ሲል ይገልጻል።

ተደጋጋሚ እገዳዎች

የሂውማን ራይትስ ዋች የምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ፌሊክስ ሆርን በኬንያ ፖሊስ እና በኢትዮጵያ ኤምባሲ መካከል ጠንካራ ግንኙነት መኖሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ሁለቱ አካላት በጋራ በመሆን ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በተደጋጋሚ ጊዜ ሲያንገላቱ፣ ሲያስፈራሩ ወይንም በዘፈቀደ ሲያስሩ እንደነበር ሂውማን ራይትስ ዋች መረጃዎች አሉት" ይላሉ።

"የኦሮሞ ማህበረሰብ አባላት ተሰባስበው ኢሬቻን እንዳያከብሩ መከልከሉ፤ ስደተኞችን የማስፈራራትና የማንገላታት አዲሱ ስትራቴጂ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

ድሪብሳ የሂውማን ራይትስ ዋች ጥናት ትክክል ነው ይላል። እሱ እንደሚለው የመሰብሰብ መብታቸውን ለኢሬቻ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይም ለመገናኘት ተቸግረዋል።

"ማህበራችንን በኬንያ የማህበረሰብ ህግ መሠረት አስመዝግበን ፈቃዱን በየወቅቱ ብናድስም የመሰባሰብ መብታችንን ተከልክለናል" ይላል ድሪብሳ።

የኃላፊዎች ምላሽ

የኢሬቻ በዓልን ለማክበር ከየትኛውም ድርጅት ጥያቄ እንዳልቀረበላቸው በኬንያ የኢትዮጵያ አምበሳደር ዲና ሙፍቲ ለቢቢሲ አስታውቀዋል። የኬንያ ፖሊስ ፈቃድ ስለመከልከሉ ምንም እንደማያውቁም ገልጸዋል።

በቅርቡ ሂውማን ራይትስ ዋች የኬንያ ባለስልጣናትና ኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ በመሆን ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ከማንገላታት ባለፈ ለኢትዮጵያ አሳልፈው ይሰጣሉ ለሚለው ሪፖርት አምባሳደሩ ምላሽ ሰጥተዋል።

"እኛ ማንንም ከኬንያ አልወሰድንም፤ ለኬንያም አሳልፈን አልሰጠንም። በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት አጠናክረን ለመቀጠል እንሰራለን። ይህ ልብወለድ ነው" ብለዋል።

የናይሮቢ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የጊጊሪ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊና ብሔራዊ የፖሊስ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊን ለማናገር ሙከራ ቢደረግም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።