ሮቦቶችን ሥነ-ምግባር ማስተማር

ሥነ-ምግባር የተላበሱ ሮቦቶች Image copyright Getty Images

ሮቦቶች ወይም ሰው-ሠራሽ ማሽኖች በራሳቸው ውሳኔ ሲወስኑ ማየት የተለመደ አይደለም። ነገር ግን ይህን ህልም የሚመስል ነገር እውን የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ይላሉ ተመራማሪዎች። ግን እንዴት ሆኖ ማሽን አመዛዝኖ ውሳኔ መስጠት ይቻለዋል?

የቢቢሲው ዴቪድ ኤድሞንድስ ከዶ/ር ኤሚ ሪመር ጋር በመኪና ጉዞ ላይ ነው። ደንገት ዶ/ር ኤሚ መኪናው ላይ ያለን 'ስክሪን' ተጫነች። ከዛም መኪናው ያለማንም መሪነት በራሱ መጓዝ ጀመረ። የትራፊክ መብራት ላይ ቆም ካለ በኋላ አደባባዩን ዞሮ ቦታ ፈልጎ በእርጋታ ቆመ።

መሪ የጨበጠ ሰው በሌለበት መኪና መጓዝ ለመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች እጅግ አስፈሪ ነበር ይላል ዴቪድ። ነገር ግም መኪናው ሁሉን ነገር በሥርዓቱ ሲከውን በማየቴ ተረጋጋሁ ሲል ያክላል።

የ29 ዓመቷ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ዶ/ር ኤሚ፤ ጃጉዋር ላንድ ሮቨር የተሰኘው መኪና አምራች ኩባንያ ያለ አሽከርካሪ የሚንቀሳቃስ መኪና ለመሥራት በሚያደርገው ምርምር ላይ ዋና ኢንጂነር በመሆን እየሠራች ትገኛለች።

እንደዶክተሯ ከሆነ መሰል አሽከርካሪ-አልባ መኪናን የዛሬ አስር ዓመት ገደማ መንገድ ላይ ማየት ብርቅ አይሆንም።

እርግጥ ነው ለዚህ ህልም መሳካት በርካታ መካኒካዊ ጉዳዮች መፈታት አለባቸው። ከዛ በላይ አሳሳቢው ነገር ግን ማሽኖቹን ሥነ-ምግባር ማስተማር ነው።

ወደፊት አሽከርካሪ-አልባ መኪኖች ጥቅም ላይ መዋል ሲጀምሩ ወዴት መዞር እንዳለባቸው፣ አደጋን እንዴት መቀነስ እንዳለባቸው፣ ወይም ማስወገድ እንዳለባቸው አመዛዝነው ውሳኔ መስጠት ይኖርባቸዋል።

መንገድ ላይ እክል ቢያጋጥም መኪናው ውስጥ ካለው ሰው እና ውጭ ካለው ሰው የቱን ማዳን አለባቸው? ከተሳፋሪው ይልቅ ለመንገደኛ ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጥ መኪና ይግዙ ቢባሉስ ይገዛሉ?

ይህንን ውሳኔስ የሚወስነው ማነው? መንግሥት? አምራቾች? እርስዎ ተጠቃሚው? ብዙ መሰል ጥያቄዎች መመለስ ይኖርባቸዋል ባይ ናቸው ተመራማሪዎቹ።

እኒህንና ሌሎች ጉዳዮች በጥልቀት ለመመርመር የሚረዳው ዘዴ 'ማሽን ለርኒንግ' ወይም ማሽኖችን ማስተማር የተሰኘው ፅንሰ-ሃሳብ ነው።

ሱዛን አንደርሰን የፍልስፍና ባለሙያ ስትሆን ባለቤቷ ማይክል አንደርሰን ደግሞ የኮምፒዩተር ሳይንቲስት ነው። እነሱ እንደሚያምኑት ማሽኖችን ሥነ-ምግባር ለማስተማር ዋነኛው መላ ሮቦቶቹ የተጫነላቸውን ፕሮግራም ሁኔታዎች ላይ እንዲተገብሩት ማስቻል ነው።

'ኬርቦትስ' የተሰኙት ሮቦቶች ለምሣሌ ሕመም ላይ ያሉና እርጅና የተጫጫናቸውን ሠዎች ለማገዝ የተሠሩ ናቸው። እኚህ ሮቦቶች ወደፊት አመዛዝነው ውሳኔ መወሰን ደረጃ ላይ መድረሳቸው አይቀሬ ነው። ቲቪ ከማብራት እና ምግብ ከማቅረብ የዘለለ ሥራ መሥራት መጀመራቸውም የማይቀር ነው።

ሱዛንና ማይክል እንደሚሉት ሮቦቶች ሁኔታን ተመርኩዘው ውሳኔ እንዴት መስጠት እንዳለባቸው በተዳጋጋሚ ከተማሩ ከሰው ልጅ የበለጠ ውሳኔ የመስጠት ደረጃ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ።

"እጅጉን ሥነ-ምግባራዊ የሆነ ውሳኔ የመስጠት ደረጃ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ አምናለሁ" ትላለች ሱዛን።

Image copyright Getty Images

ይህም ቢሆን ግን ማሽኖችን ማስተማር የተሰኘው ፅንሰ-ሃሳብ የራሱ ችግሮች ይዞ መምጣቱ አይቀርም። አንደኛው ነገር ማሽኖች የተሳሳተ ነገር ሊማሩ መቻላቸው ነው። ለጥቆም የከፋ ችግር የሚሆነው ወደፊት ማሽኖች እንዴት ያለ ባህሪ ሊያመጡ እንደሚችሉ መገመት አለመቻሉ ነው።

ዋናው ነገር ግን እንደተመራማሪዎቹ አባባል ሮቦቶች መሰል ባህሪዎችን ማሳየት ከጀመሩ መቆጣጠር የሚያስችለን ቁልፍ በእጃችን መኖሩ ነው። ሮቦቶች ላጠፉት ጥፋት ወንጀለኛ ብለን ልንከሳቸው አለመቻላችን ለሚጠፋው ጥፋት እኛው ተጠያቂ መሆናችን ማሳያ ነው።

ደጉ ነገር ግን አሽከርካሪ አልባ መኪኖች አይሰክሩም ወይም አይደክማቸውም፤ ተሳፋሪ ላይ ለመጮህም አይዳዳቸውም።

በየዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በመኪና አደጋ ሕይወታቸውን ያጣሉ፤ በአብዛኛው በአሽከርካሪ ወይንም በመንገደኛ ጥፋት ነው። በአሽከርካሪ አልባ መኪናዎች በመታገዝ ይህንን አደጋ መቀነስ በራሱ ትልቅ ድል ነው።

ሮቦቶች ዳኛ ሆነው ያልተጓደለ ፍርድ ሊሰጡም ይችላሉ በማለት ሃሳባቸውን ይሰንዝራሉ ተመራማሪዎች።

በሰው ልጅ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያፈርስ ከንቱ ሃሳብ በማለት የሮቦቶችን ማመዛዘን ጉዳይ ውድቅ የሚያደርጉት ደግሞ የለንደኑ ኪንግስ ኮሌጅ ፕሮፌሰር ጆን ናቸው።

"የሰው ልጅ ሁኔታዎችን አገናዝቦ ትክክለኛውን ፍርድ መበየን ሲችል በማሽን የታገዘ የፍርድ ሥርዓት ማለት ምን የሚሉት ነው?" ሲሉ ይከራከራሉ።

ዶ/ር ኤሚ ስለ ተሽካርካሪ-አልባ መኪና ዕድገት እጅግ ተደስታለች። ሕይወት መታደጉ ብቻ ሳይሆን መጨናነቅና የበካይ ጋዝ ልቀትንም ለመከላከል ፍቱን መፍትሄ ነው ትላለች።

ሮቦቶች ወጣም ወረደ ወደፊት የሰው ልጅ ሥራ እየተረከቡ መምጣታቸው ስለማይቀር ሥነ-ምግባር ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል የሚለው ሃሳብ ግን ሚዛን እየደፋ ነው።