ስፔን ካታሎንያን በቁጥጥሯ ስር ልታደርግ ነው

ካታሎናውያን Image copyright AFP

የካታሎን መሪ የግዛቲቱን ነፃነት እንደሚያውጁ መዛታቸውን ተከትሎ ስፔን የካታሎን ራስ-ገዝ አስተዳደርን ከቅዳሜ ጀምሮ ልታግድ ነው።

የስፔን መንግሥት እንዳለው ማዕከላዊው አስተዳደር የካታሎንያን ግዛት እንዲያስተዳድር የሚፈቅድለትን የሃገሪቱን ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 155 ተግባራዊ ለማድረግ ሚኒስትሮች ይሰበሰባሉ።

ስፔን በግዛቲቱ ላይ የምትፈፅመው ''ጭቆና የሚቀጥል ከሆነ'' አወዛጋቢ የነበረውን ሕዝበ-ውሳኔ በመደገፍ የካታሎንያ ፓርላማ ለነፃነት ድምፅ አንደሚሰጥ የካታላን መሪ ተናግረዋል።

አንዳንዶች ይህ እርምጃ አለመረጋጋትን ሊያስከትል ይችላል ብለው ሰግተዋል።

''የካታሎንያ ራስ-ገዝ አስተዳደርን በተመለከተ በሕገ-መንግሥትቱ አንቀፅ 155 ላይ የሰፈረውን መሰረት በማድረግ የስፔን መንግሥት ሕግን ለማስከበር መስራቱን ይቀጥላል'' ሲል የመንግሥት መግለጫ አሳውቋል።

በካታሎንያ አስተዳደር በኩል ያለውን የአብሮ መኖርና ምጣኔ ሃብታዊ መዋቅር ስልታዊና በታሰበበት በተሰበበት ሁኔታ ተቋማዊ ፍጥጫን ለመፍጠር የታለመውን ድርጊት የስፔን መንግሥት እንደሚያወግዘው ገልጿል።

መግለጫው ጨምሮም ''ሕገ-መንግሥታዊውን ደንብ ለማስከበር የስፔን መንግሥት አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ አደልም'' ሲል አስጠንቅቋል።

ይህ የሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 155 እስካሁን ተግባራዊ ሆኖ ባያውቅም፤ ቀውስ በሚያጋጥም ጊዜ ማዕከላዊው መንግሥት የቀጥታ አስተዳደርን እንዲተገብር የሚፈቅድለት ነው።

የስፔን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕገ-ወጥ ነው ያለውና የካታሎንያ መሪዎች ለነፃነት ድጋፍ አግኝተንበታል ባሉት አወዛጋቢው ሕዝበ-ውሳኔ ምክንያት የማድሪድ እና የባርሴሎና ፖለቲከኞች ከባድ ፍጥጫ ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል።

ተያያዥ ርዕሶች