ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ተመለስዉ በመሄድ ላይ ናቸው

ስደተኞች Image copyright KHALED FAZAA

ወጣት አባዲ ባደገበት መንደር 'እነ እገሌ ሣኡዲ አረቢያ ሄደው አለፈላቸው' የሚለውን ተደጋጋሚ ወሬ ሲሰማ ነው ያደገው። እናም እሱም እንደ ሌሎቹ 'አልፎለታል' ተብሎ እንዲወራለት የየመን በረሃን አቋርጦ ሳዑዲ አረቢያን የረገጠው የስምንተኛ ከፍል ተማሪ ሳለ ነበር።

የ18 ዓመት ወጣት ሆኖ በብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ዘንድ ጥሩ ገንዘብ የሚገኝባት ሃገር ተደርጋ ወደምትታሰበው ሳዑዲ አረቢያ የተጓዘው አባዲ፤ ነገሮች እንዳሰባቸው ሳይሆኑ የረገጣት ጅዳ ወህኒ ቤት አዘጋጅታ ጠበቀችው።

ጅዳ ወህኒ ቤት ውስጥ ለሦስት ዓመታት በታሰረበት ወቅትም ብዙ ስቃይ እና መከራ እንዳሳለፈ የሚናገረው ወጣቱ አብዲ፤ የሌሎች ሃገር ዜጎች በኤምባሲዎቻቸው አማካኝነት የጤና ሁኔታቸው እና የፍርድ ቤት ጉዳያቸው ክትትል ሲደረግላቸው ኢትዮጵያውያን ግን አንድም ጠያቂ እንዳልነበራቸው ያወሳል።

ከዚህ የተነሳም በወህኒ ቤቱ ታስረው የነበሩት ኢትዮጵያውያን 'ለመሆኑ ሃገር አለን ወይ?' እስከ ማለት ደርሰው እንደነበር ይገልጻል።

አባዲ 'ምንም እንኳ ህገወጥ ስደተኞች ብንሆንም እንደ ዜጎች ግን ከኤምባሲያችን አስፈላጊው ክትትል ሊደረግልን ይገባ ነበር' ባይ ነው።

ቢቢሲ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራርያ ለመጠየቅ ሳዑዲ አረቢያ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተደጋጋሚ ቢደውልም ሳይሳካ ቀርተዋል።

'በቴሌቭዥን የሚወራ ውሸት ነው'

ተክሊት ብርሃነም ሌላኛው በለጋ እድሜው ሣኡዲ አረቢያን የረገጠ ኢትዮጵያዊ ነው። በሳዑዲ አረቢያ መንግሥት አዋጅ መሰረትም ሀገሪቱን ለቆ ኢትዮጵያ ከተመለሱት መሃከል ነው።

ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ መንግሥት በመገናኛ ብዙሃን አመካኝነት ለተመላሾቹ የተለያዩ የሥራ እድል እና የብድር አገልግሎት እንደሚሰጥ የተነገረውን ተስፋ አድርጎ ሀገሩ መግባቱን ይናገራል። ወደ ትውልድ ስፍራው ተጉዞ ያገኘውን ግን ተስፋ አስቆራጭ እንደነበር ለቢቢሲ በሰጠው ቃለመጠይቅ ገልጿል።

አንድም የመንግሥት አካል ያነጋገረው እንደሌለ እና በቴሌቭዥን የሰማቸው የመንግሥት ሃሳቦችን መሬት ላይ አላገኛቸውም። ምንም እንኳ ተመልሶ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ቢገባ ህይወቱ አጣብቂኝ ውስጥ እንደምትወድቅ ቢረዳም፤ ከዚህ በፊት ያለፋቸውን አደገኛ የጉዞ ውጣ ውረዶች አልፎ ተመልሶ ሳዑዲ አረቢያ መግባቱን ይናገራል።

ከዚህ የተነሳም ተክሊት 'ቴሌቭዥን ላይ የሚወሩት ወሸት ናቸው' ይላል።

Image copyright TONY KARUMBA

በአዋጁ ምክንያት ወደ ሃገሩ ያልተመለሰው እና ተክሊት ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንዲገባ ለደላሎች 13 ሺህ ብር መክፈሉን የሚናገረው ታላቅ ወንድሙ ፍስሃ፤ ሌሎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የነበሩት ሁለት እህቶቹ ተመልሰው ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት በየመን በረሃ እንደሚገኙ ይናገራል።

በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንደሚባለው፤ ፍስሃ የመን ላይ በደላሎች ተይዘው የሚገኙ እህቶቹን ለማስለቀቅ በአማካይ እስከ 50 ሺህ ብር መክፈል እንደሚጠበቅበት በመግለጽ ሁኔታው አጅግ እንዳስጨነቀው በምሬት ይገልጻል።

ተመላሾቹ ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተጨማሪ እድሜያቸው 18 ያልደረሱ ልጆችን ሳይቀር ይዘው በመንገድ ላይ ናቸው።

በዚህም ሳቢያ ደግሞ የኢትዮጵያውያን ህይወት በየመን እና በሳዑዲ አረቢያ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ስደተኞቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሃገር ቤት ስላለው ሁኔታ እየደወሉ እነደሚጠይቁ እና ተስፋ የሚሰጥ ነገር በማጣታቸው፤ ላለመመለስ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን እነዚህ ወጣት ስደተኞች የይገልፃሉ።

በዚህ ጉዳይ ላይ በሀገር ደረጃ ያለውን አንድምታ ለመጠየቅ ጉዳዩ ወደሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ብንደውልም ሳይሳካ ቀርቷል።

እኛ ይብሳል!

በሳዑዲ ጂዛን አካባቢ በሺዎች የሚቆጠሩ መጨረሻቸውን የማያውቁ ኢትዮጵያውያን እስረኞች እንደሚገኙ የሚናገረው ወጣት አባዲ፤ ስደተኞች በየቀኑ ግርፋት እና ግድያ እንደሚደርሳቸው ለቢቢሲ ተናግሯል።

'አሁን በስልክ ሳናግርህ ራሱ ሀዘን ላይ ተቀምጠን ነው' የሚለው አብዲ በቅርቡ አንድ ኢትዮጵያዊ በሳዑዲ አረቢያ ታጣቂዎች ተገድሎ አስከሬኑን ወደ ሀገር ቤት ለመላክ ብር በማዋጣት ላይ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ተስፋ ስላጡ እንጂ የስደት ኑሮን ወደዉት እንዳልሆነ የሚናገሩት ወጣቶቹ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወት በየበረሃው እየተቀጨ መሆኑን በጥልቅ ሀዘን ይናገራሉ።

ይህ ጉዳይ ፈጣን ምላሽ የሚያሻው ነው፤ በማለት የሁኔታው አሳሳቢነት የሚገልጹት ወጣቶቹ 'የሀገራችን መገናኛ ብዙሃን ስለ የኤርትራውያን ስደት ያወራሉ እንጂ፤ ችግሩ እኛ ላይ ይብሳል' ብለዋል።

ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በርካታ ወጣቶች ሥራ ወደ ሳዑዲ አረቢያ እና ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት በአደገኛ መንገድ ተጉዘው ለችግር ይዳረጋሉ።

በህገወጥነት ተመልሰው የመጡት ሳይቀር ተመልሰው ወደ መጡበት እየተጓዙ ነው።