የአውሮፓ ህብረት በካታሎንያ ቀውስ ላይ ጣልቃ አንገባም አለ

የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአውሮፓ ህብረት አመራር ጋር Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአውሮፓ ህብረት አመራር ጋር

የአውሮፓ ካውንስል ፕሬዚዳንት ዶናልድ ታስክ በካታሎንያ ያለውን አሳሳቢ ቀውስ ለማርገብ የአውሮፓ ህብረት ጣልቃ እንደማይገባ በግልፅ ተናግረዋል።

"ለማስማማትም ሆነ፤ ዓለም አቀፍ እርምጃ ለመውሰድ ምንም አይነት ቦታ የለም" ብለዋል።

ይሄንንም ንግግር ያደረጉት ከአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ጂን ክላውድ ጀንከር ጋር በህብረት ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው።

ባለፈው መስከረም 21 በተደረገው ሕዘበ-ውሳኔ ካታሎናውያን ከስፔን ለመገንጠል ቢመርጡም፤ በስፔን መንግስት ዘንድ ተቀባይነትን ባለማግኘቱ ከፍተኛ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎችን አስተናግዷል።

ይህ የዶናልድ ታስክ ንግግር የተሰማውም የስፔን መንግስት ራስ ገዝ በሆኑ የካታሎንያ ግዛቶች ላይ የቀጥታ አገዛዝን እጭናለሁ ካለ በኋላ ነው።

" በተለያዩ ጉዳዮች ከስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪያኖ ራጆይ ለዘለቄታው እየተነጋገርንም ነው" ካሉ በኋላ " በስፔን ውስጥ እየተካሄደ ያለው አሳሳቢ ጉዳይ የተደበቀ አይደለም ነገር ግን ያለን አቋም ግልፅ ነው። " ብለዋል።