"ማንም ታሸንፋለች ብሎ የገመተ አልነበረም". . . ደራርቱ ቱሉ ከባርሴሎና ኦሎምፒክ 25 ዓመታት በኋላ

Daraartuu fi Elenaa Meyeer dorgommiin booda harka walqabatanii Image copyright PASCAL PAVANI/AFP/Getty Images

ቤቷ ውስጥ የተደረደሩትን ሜዳሊያዎች በመመልከት ይህች አትሌት በሥራዋ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነች መናገር ይችላል።

ድሏን የሚያወጁ፣ አሸናፊነቷን የሚዘክሩ፣ ታሪኳን የሚተነትኑ ወርቆች፣ ብሮች እና ነሃሶች በዓይነት በዓይነቱ ተሰድረዋል። ሃገሯ ኢትዯጵያን በ3 ሺህ ፣ በማራቶን እና በሃገር አቋራጭ እንዲሁም አህጉረ አፍሪካን ያስጠራችባቸው ሜዳልያዎች።

የልጅነት ህልሟ አስተማሪ መሆን ነበር። እነሆ ዛሬ ሃገር ያስጠራች አትሌት እና ኢንቨስተር ለመሆን ችላለች።

ባርሴሎና ሲታወስ

"ማንም ታሸንፋለች ብሎ የገመተ የለም። የሁሉም ዓይን በደቡብ አፍሪካዊቷ አትሌት ኤሌና ሜየር ላይ ነበር" ትላለች ደራርቱ የዚያን ጊዜ የነበረውን ስታስታውስ።

ከኤሌና ቀጥሎ የአሜሪካ እና አየርላንድ አትሌቶች ለማሸነፍ ቅድሚያ ግምት የተሰጣቸው ሯጮች ነበሩ። ደራርቱን ያስተዋላትም ያስታወሳትም አልነበረም።

ነገር ግን ሳይታሰብ ተፈትልካ በመውጣት ለሃገራ አልፎም ለአፍሪካ ወርቅ አመጣች፤ በ10 ሺህ ሜትር ወርቅ ያመጣች የመጀመሪያዋ ሴት ጥቁር አፍሪካዊት ለመሆንም በቃች።

"የባርሴሎና ኦሊምፒክ የሕይወቴን አቅጣጫ የቀየረ ነበር። ከአስራለቃነት ወደ ሻለቃነት ደረጃ አደግኩኝ፤ ደሞዜ ከ200 ብር ወደ 600 ብር አደገ፤ ዝናየም ናኘ" ስትል ድሉ ያመጣላትን በረከት ትናገራለች።

ወርቅ ሜዳሊያው የእርሷና የሃገሯ ብቻ ሳይሆን የመላ ጥቁር ህዝቦች ድልም ነበር።

ከደራርቱ ድል በኋላም በእርሷ አሸናፊነት መንፈስ የተቃኙ በርካታ ሴት ኢትዮጵያዊያን ሯጮች መታየት ጀመሩ።

ደራርቱና ፈረስ ግልቢያ

ደራርቱ ለፈረስ ግልቢያ ያላት ጥልቅ ፍቅር ከልጅነቷ ጀምሮ የነበረ ነው። ከአባቷ ጋር በመሆን ትጋልብ እንደነበረ ታስታውሳለች።

"አባቴ 'ጆቴ' የተባለ ፈረስ ነበረው። ጠመንጃ የተባለ ሥፍራ አባ ጆቴን እየጋልብኩ ከብቶችን እጠብቅ ነበር" ትላለች ደራርቱ።

ነገር ግን ወደ አዲስ አበባ ከመጣች በኋላ ፈረስ ጋልባ እንደማታውቅ እና የልጅነት ታሪክ ሆኖ እንደቀረ ትናገራለች ደራርቱ።

ደራርቱ እና ኦምፒክ ኮሚቴ

አሁን አሁን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ በአትሌቲክስ ዘርፍ የምታገኘው የሜዳሊያ ቁጥር እየቀነሰ እንደመጣ ብዙ ሰዎች ይናገራሉ።

በብራዚሉ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በ1 ወርቅ፣ 2 ብር እና 5 ነሃስ ከዓለም 44ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በቅርቡ በተከናወነው የለንደን ዓለም ቻምፒዮና ከታሪካዊ ተቀናቀኟ ኬንያ አምስት ደረጃ ተንሸራታ 5 ሜዳሊያ ይዛ ተመልሳለች።

''ከእነዚህ ሁለት ውድድሮች ብዙ ተምረን በጣም ጠንከረን መሥራት አለብን" የምትለው ደራርቱ "አትሌቶቻችን ያለባቸውን ችግር በማጣራት መቅረፍ ይኖርብናል" ስትል ታክላለች።

ደራርቱ አባል የሆነችበት የኦሊምፒክ ኮሚቴ ያሉትን ችግሮች ቀርፎ በቶኪዮ ኦሊምፒክ አመርቂ ውጤት ለማምጣት ከወዲሁ ሥራ መጀመሩን ለቢቢሲ ተናግራለች።

የብዙ አትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው በቆጂ የአትሌቲክስ ማዕከል ለመግንባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ነግራናለች ደራርቱ።

ኢንቨስትመንት

"ከአትሌቲክስ ባፈራሁት ገንዘብ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራሁ ነው፤ ራሴንና ቤተሰቤን ከመርዳት አልፌ ማለት ነው። በርካታ የሥራ ዕድል በመፍጠር ለሃገሪቱ ዕድገት የበኩሌን አስተዋፅኦ እያበረከትኩ ነው" በማለት ደራርቱ ለቢቢሲ ተናግራለች።

"ወደ ኢንቨስትመንት ከመምጣቴ በፊት አትሌቲክስ በጣም ከባዱ ዘርፍ ነው ብዬ አስብ ነበር። አሁን ግን ሁሉም ሥራ የራሱ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ አምኛለሁ" ባይ ናት።

አሁን ላይ ደራርቱ በአዲስ አበባ እና አዳማ ከተሞች በሆቴል እና የንግድ ህንፃ ግንባታ ተሰማርታ ትገኛለች።