ኦባማ እና ቡሽ ትራምፕን ተቹ

Image copyright Getty Images/Reuters

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ባራክ ኦባማና ጆርጅ ቡሽ የዶናልድ ትራምፕን አመራር በሚተች ሁኔታ በሃገሪቱ ያለውን ውቅታዊ ፖለቲካ አንደሚያሳስባቸው ተናገሩ።

ባራክ ኦባማ አሜሪካውያን ''የመከፋፈል'' እና ''የፍርሃት'' ፖለቲካን እንዲቃወሙ ጥሪ ሲያቀርቡ ጆርጅ ቡሽ ደግሞ በፖለቲካ ውስጥ ''ማሸማቀቅ እና ጭፍን ጥላቻ'' ያሉትን ተችተዋል።

ሁለቱም የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች ንግግር ያደረጉት በተለያዩ ቦታዎች ሲሆን የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ስም ግን አልጠቀሱም።

ቀደም ሲል ሁለቱን ፕሬዝዳንቶች በመተቸት የሚታወቁት ትራም ምላሻቸው ምን እንደሚሆን እየተጠበቀ ነው።

በአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች በሥልጣን ላይ ያለን ፕሬዝዳንት በይፋ መተቸት ብዙም የተለመደ አይደለም።

ኦባማ ግን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኦባማኬር የተባለውን የጤና አገልግሎት ለማስቆም ጥረት ሲያደርጉ፣ አወዛጋቢው የሆነውን በተወሰኑ የሙስሊም ሃገራት ዜጎች ላይ የጉዞ እገዳ ሲጥሉና ከፓሪስ የአካባቢ ጥበቃ ስምምነት ለመውጣት ሲወስኑ በፕሬዝዳንቱ ላይ ትችት ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

ኒውጀርሲ ውስጥ በተከናወነው የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዝግጅት ላይ፤ ኦባማ አሜሪካዊያን ''የመከፋፈልና የፍርሃትና ፖለቲካን እንደምንቃወም ለዓለም ማሳየት አለብን።''

ጨምረውም ''ከዘመናት በፊት በተደጋጋሚ ያጋጠመንን ያረጀ የክፍፍል ፖለቲካን ደግመን ማየት የለብንም። አሁን የምናየው ይህን መሰል ፖለቲካ ቀርቷል ብለን እናስብ ነበር። ይህ ድርጊት 50 ዓመት ወደ ኋላ ይመልሰናል'' ብለዋል።

በሌላ ስፍራ ላይ ባደረጉት ንግግርም ''የአጭር ጊዜ ድጋፍ ለማግኘት ሆን ብሎ ሰዎችን ማስቆጣት እና ተለየ ሃሳብ ያላቸውን ሰዎች ማንቋሸሽን'' ተቃውመዋል።

በሰዓታት ከኦባማ ቀደም ብለው ኒው ዮርክ ውስጥ ንግግር ያደረጉት ጆርጅ ቡሽ ደግሞ ''የሃገራችን ፖለቲካ ለሴራ ንድፈ ሃሳብ እና ለፈጠራ ወሬ የተጋለጠ ይመስላል። ዘረኝነት እየተጠናከረ ነው።''

''በተለይ በወጣቱ በኩል ለዲሞክራሲ የነበርው ድጋፍ እየላላ መሆኑን አንዳንድ ምልክቶች ይታያሉ'' ብለዋል ቡሽ።

በተጨማሪም ''የምናደርገው ውይይት በተደጋጋሚ ጭካኔዎች ምክንያት ትኩረትን ተነፍገዋል''

''አንዳንድ ጊዜ የሚከፋፍሉን ነገሮች አንድ አድርገው ከሚያስተሳስሩን የበለጠ ኃይል ያላቸው ይመስላሉ" ሲሉ ቡሽ ተናግረዋል።

ሁለቱም የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች እስካሁን በትራምፕ ፖሊሲዎች ላይ በይፋ ትችት ከመሰንዘር ተቆጥበው ቆይተዋል።

ፕሬዝዳት ትራምፕ ግን በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ባራክ ኦባማን እና ጆርጅ ቡሽን ''በአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ታሪክ መጥፎዎቹ ሳይሆኑ አይቀሩም'' በማለት ክፉኛ ይተቿቸው

ትራምፕ የፕሬዝዳንትነት መንበሩን ከያዙ በኋላ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በሚሰጧቸው ውዝግብን በሚጋብዙ አስተያየቶቻቸው የተነሳ በዲሞክራትና ሪፐብሊካኖች መካከል ተቃውሞን እያስተናገዱ ነው።

ትራም ለሚገጥማቸው ተቃውሞዎች የመገናኛ ብዙሃንን ''ከሰራሁት መልካም ነገር ይልቅ ሃሰተኛ ዜና ላይ ያተኩራሉ'' በማለት ይወቅሳሉ።