አቤ ሰሜን ኮሪያን እመክታለሁ አሉ

የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ

የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ እሁድ በተደረገው ምርጫ እንደሚያሸንፉ ካረጋገጡ በኋላ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ባለው ፍጥጫ ዙሪያ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስዱ ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ ከጊዜው ቀደም ብለው ምርጫ እንዲካሄድ የጠሩት ከሰሜን ኮሪያ በኩል ያለውን ስጋትና ሌሎች ጃፓንን የገጠሟትን ችግሮች ለማስወገድ ድጋፍ ለማግኘት ነው።

የጃፓን መገናኛ ብዙሃን እነደዘገቡት በጠቅላይ ሚኒስትር አቤ የሚመራው ጥምረት በፓርላማው የነበረውን የሁለት ሦስተኛ የበላይነት ማስጠበቅ ችሏል።

ይህም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጃፓን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ያፀደቀችውን በየትኛውም ፍጥጫ ውስጥ እንዳትገባ የሚከለክለውን ሕገ-መንግሥት ለማሻሻል በሩን ይከፍትላቸዋል።

ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጃፓን መከላከያ ኃይል መደበኛ ትኩረት እንዲያገኝ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ ይህም የጦር ሠራዊቱ እንዲጠናከር የሚያደርግ በመሆኑ ወታደራዊ ግንባታን መልሶ ያመጣል በሚል ትችት ተሰንዝሮባቸዋል።

ከምርጫው በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ''ቃል በገባሁት መሰረት ቀዳሚው ሥራዬ የሚሆነው ሰሜን ኮሪያን ጠንከር ባለ ሁኔታ መጋፈጥ ነው። ለዚህም ጠንካራ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል'' ብለዋል።

ከሁለት ወራት በፊት ፖለቲካዊ ቀውስ ገጥሟቸው የነበሩት ሺንዞ አቤ፤ ሰሜን ኮሪያ በጃፓኗ ደሴት ሆካይዶ ላይ ያለፉ የሚሳኤል ሙከራዎችን ካደረገች በኋላ ከፖለቲካዊ ቀውሱ ለማንሰራራት ችለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ምርጫ ማሸነፋቸው ፓርቲያቸው በቀጣይ በሚያደርገው የመሪ ምርጫ ላይ ለሦስተኛ ጊዜ የመመረጥ እድላቸውን ከፍ ያደርግላቸዋል ተብሏል።

ይህ ከሆነም ሺንዞ አቤ ለረዥም ጊዜ ጃፓንን የመሩ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን እድልን ያገኛሉ።