የቅኔው ተማሪ በአሁኑ ዘመን

አምሃ ይርዳው
አጭር የምስል መግለጫ አምሃ ይርዳው

በርካታ ቀዳሚ የኢትዮጵያ ምሁራን መነሻቸው ከአብነት ትምህርት ቤት መሆኑ ተደጋግሞ ይወሳል፤ የአብነት ትምህርት ከዘመናዊ ትምህርት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የወትሮ ሚናውን ማጣቱ ቢስተዋልም፤ አሁንም ጥቂት ለማይባሉ ወጣቶች ምርጫ መሆኑ አልቀረም።

አምሃ ይርዳው በባህር ዳር ከተማ የጣና ሐይቅ ዳርቻ በሚገኘው የሽምብጥ ሚካዔል ቤተክርስትያን ውስጥ የቅኔ ተማሪ ነው።

ዘመናዊ ትምህርቱን አቋርጦ የአብነት ትምህርት የጀመረው ከአራት ዓመት በፊት ነበር። በወቅቱ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነበር።

ቀዳሚ የአብነት ትምህርቱን መከታተል የጀመረው በትውልድ ቀዬው ደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ በምትገኝ ቤተ ክርስትያን ውስጥ ነው።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ ደግሞ ለከፍተኛ ደረጃ ትምህርት ወደ ሽምብጥ ሚካዔል መጥቷል።

ወላጆቹ ፊቱን ወደኃይማኖታዊው የአብነት ትምህርት ማዞሩ ብዙም ባያስከፋቸውም ለውሳኔው የሰጡት ድጋፍ ግን የኋላ ኋላ ወደዘመናዊ ትምህርት መመለሱ እንደማይቀር ተስፋ ከማድረጋቸው ጋር የሚያያዝ ነው።

"የቅኔ ትምህርት የቀመሰ ሰው አስኳላው ላይ ጎበዝ ስለሚሆን፤ አይዞህ በርታ በኋላ ለቋንቋ ያግዝሃል ነው ያሉኝ" ይላል።

እርሱ ግን ወደ 'አስኳላ' የመመለስ ውጥን የለውም፤ "ምን ይሠራልኛል?" ይላል።

ሁለቱ እህቶቹ በአንፃሩ አትኩሮታቸውን ለዘመናዊ ትምህርት ሰጥተዋል። "አምስተኛና አስረኛ ክፍል ደርሰዋል፤ አግብተው ትምህርቱን ካልተውት ወይ መምህር ወይ የመንግስት ሰራተኛ ይሆናሉ"ይላል።

ታላቅ ወንድሙ ነጋዴ ሲሆን የእርሱን ፈለግ የመከትል ኃሳብ ሽው ብሎበት እንደማያውቅ ይናገራል።

"የቅኔ ትምህርት ሌሎች የአብነት ትምህርቶች ሳይጨመሩበት ብቻውን ለጠነከረ ተማሪ ሁለት ዓመት ይፈጃል" ሲል ለቢቢሲ ያስረዳል።

እርሱን እንደጨረሰ አቋቋም ለመማር ብቁ ይሆናል። ከዚያ "አንዲት ደብር ፈልጌ መቀጠርና ያው መሪጌታ መሆን ነው የምሻው" ይላል።

የቅኔ ትምህርትን አስቸጋሪ ሆኖ እንዳገኘው ባይክድም "የዕውቀት በርን የሚከፍት ነውና ቢለፉበትም አይገድም"ይላል።

ከመምህሩ የሚሰጠውን ትምህርት ከተከታተለ በኋላ ግላዊ ጥናቱን ለማከናወን ብዙ ጊዜ በጣና ሐይቅ ዳርቻ ላይ ያደፍጣል።

ትምህርቱና ጥናቱ በየዕለቱ ብዙ ጊዜውን የሚወስድበት መሆኑ ግን ራሱን የሚደጉምበት ስራ እንዳይሰራ አቅቦታል።

ስለዚህም አሁን ለሆዱ ፍጆታ የሚያውለውን የሚያገኘው እርጥባን በመለመን ነው።

ኑሮውን ደግሞ ቤተ ክርስትያኑን ታክከው ከተሰሩ ትናንሽ የሳር ጎጆዎች ውስጥ በአንደኛው አድርጓል።

በአንድ ጎጆ ውስጥ ከሌሎች መሰል የቅኔ ተማሪዎች ጋር አምስት ሆነው ይኖራሉ።

አጭር የምስል መግለጫ አምሃ ይርዳው

የአብነት ትምህርት መልኮች

የአብነት ትምህርት ቤቶችን "ኃይማኖታዊና ባሕላዊ እሳቤዎችን፤ እሴቶች እና ትውፊቶችን ለታዳጊዎች እንዲሁም ለአዋቂዎች" ለማስተማር የተወጠኑ የቤተ ክርስትያን የትምህርት ተቋማት ናቸው ሲሉ በዚሁ ርዕስ ላይ ጥናት ያከናወኑት አሰለፈች ገብረኪዳን ይገልጻሉ።

ትምህርቱ በዋናነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ባለቤትነት ሲተዳደር ቆይቷል።

የአብነት ትምህርት የጉባዔ ቤቶች ተብለው በሚጠሩ ልዩ ልዩ የትምህርት ዘርፎች የተከፋፈለ ሲሆን ከመካከላቸውም ንባብ ቤት፣ ዜማ ቤት፣ አቋቋም ቤት፣ ቅኔ ቤት፣ ቅዳሴ ቤት እና መፃሕፍት ቤት ይገኙባቸዋል።

እነዚህ ዘርፎች ከስነ-ኃይማኖታዊ ትምህርት በተጨማሪ የንባብ፣ የሙዚቃ፣ የስነ ግጥም፣ የፈጠራ እንዲሁም የስነ ጽሑፍ ዕውቀትን ለአጥኝዎቻቸው ያቀብላሉ።

በተለይ እንደመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ሊታይ የሚችለው የንባብ ቤት በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያናት ውስጥ እንደሚገኝ በጉዳዩ ላይ ጥናት የተከናወነባቸው ሰነዶች ያስረዳሉ።

በአገሪቱ ውስጥ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ አብያት ክርስትያናት እንዳሉ የሚገመት ሲሆን ከዚሁ ጋር የሚመጣጠን ቁጥር ያላቸው የንባብ ቤቶች አሉ።

ትምህርት ቤቶቹ ትውፊት ተጠብቆ ለመዝለቁ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሚያወሱት ተመራማሪዋ፤ ከዚህም ባሻገር የአዋቂዎችን ትምህርት በማሰራጨት ረገድ ላቅ ያለ አስተዋፅዖ እንደነበራቸው ይሟገታሉ።

አሰለፈች ከአብነት ትምህርት ልዩ መገለጫዎች መካከል ታዳጊ ተማሪዎቹ በራሳቸው ለወላጅ ፈቃድ ብዙም ሳይጨነቁ ወደአዳዲስ ስፍራዎች የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው፤ ተማሪዎቹ ይህንን በሚያደርጉበት ጊዜም ለትምህርት ያቀኑበት ማኅበረሰብ ምግብ በመቸር የሚደግፋቸው መሆኑ፤ ትምህርቱ በጥቅሉ እስከአርባ ዓመታት ያህል ሊወስድ መቻሉ እና በአብዛኛውም በአፋዊ አስተምህሮ ላይ የተንጠላጠለ መሆኑ ተጠቃሽ ናቸው ይላሉ።

ይሁንና የትምህርት ቤቶቹ ህልውና ከሚያስተዳድሯቸው አብያተ ክርስትያናት መድከምና መጠንከር ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ለፈተና ሲዳረጉ ይስተዋላሉ።

አጭር የምስል መግለጫ የአምሃ የቅኔ መማሪያ አካባቢ

የትምህርት ስርዓቱን የበለጠ ማደራጀት እንደሚያስፈልግ የሚመክሩት አሰለፈች ከቤተ ክርስትያኗ ውጭም መንግስት የአብነት ትምህርትን ለመሳሰሉ ነባርና አገር በቀል ዕውቀትን የመጠበቂያና የማስተላለፊያ ስርዓቶች ተገቢውን አትኩሮት መስጠት እንዳለበት ይገልፃሉ።

ባለፈው ነሐሴ ወር የትምህርት ስርዓቱን ለመጠበቅ እና ለመደግፍ ያስችላል የተባለ ፖሊሲ መረቀቁ ይታወሳል።

ረቂቅ ፖሊሲው ከጥልቅ የዕውቀት ማኅደርነቱ ባሻገር፤ የአገር ቅርስም ነው የተባለውን የአብነት ትምህርት የበለጠ ለማስተዋወቅ ብሎም ለማጎልመስ ያግዛል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

አምሃ የኑሮ ሁኔታው ቢሻሻል እንደማይጠላ ቢገልፅም ያን ያህል የሚጨነቅበት ጉዳይ እንዳልሆነ ግን ይናገራል።

"አባቶች እንደዚሁ አይደል የተማሩት፤ እኔ በምን አቅሜ እለያለሁ?" ይላል ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ።

ነገር ግን ከቀዳሚ የአብነት ተማሪዎች የበለጠ ፈተና እንዳለበት ይገምታል።

"ወትሮ ስንሰማ ምፅዋት ማግኘቱ ቀላል ነበር፤ አሁን ግን አንዳንዱ በጥርጣሬ ነው የሚያየን። እንዳንዴ ደግሞ ከተማውም ድምቅ ብሎ ሲያዩት ይፈታተናል።"

ተያያዥ ርዕሶች