ሙጋቤ ሹመቱን ሀገራቸው ትምባሆ አምራች ስለሆነች አይቀበሉም ነበር።

ሮበርት ሙጋቤ Image copyright Getty Images

የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ የዓለም ጤና ድርጅት የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሹመትን አገራቸው የትምባሆ አምራች ከሚባሉ አንዷ በመሆኗ ሹመቱን ለመውሰድ በጭራሽ ፈቃደኛ እንደማይሆኑ መንግስታዊው ጋዜጣ ሄራልድ የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑትን ጆርጅ

ቻራምባን በመጥቀስ ዘግቧል።

ሙጋቤ የሹመቱን ዜና የሰሙት በመገናኛ ብዙኃን ሲሆን በኦፊሴያላዊ ደረጃ ምንም ጥያቄ ያልቀረበ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ "ጉዳዩን አሳፋሪ ነው " ሲሉ ጆርጅ ቻራምባ ተናግረዋል።

ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በመሆን ሲሾሙ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ናቸው።

የዓለም ጤና ድርጅት ትምባሆ ላይ ግልፅ አቋም ያለው ሲሆን ሙጋቤም ከአገሪቷ ብሔራዊ ፍላጎት ጋር የማይጣጣም ዘመቻን በመከተል ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ የሆነውን ትምባሆን ከማብቀል፣ ከመሸጥ እንደማትቆጠብ ተናግረዋል።

ዚምባብዌ የትምባሆ ምርቷን ታቁም የሚለውን ሙጋቤ አይስማሙም "ምክንያቱም የሲጋራ አጫሾች ማጨስ ይፈልጋሉ፤ ከሲጋራ በላይ መጥፎና ገዳይ የሆኑ መጠጦች እንደነ ዊስኪና ቢራ በዓለም ይመረታሉ፤ ይሸጣሉም" በማለት ጆርጅ ቻምባራ ተናግረዋል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ በአለም ዓቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የትምባሆ አምራች ከሚባሉ አገራት ዚምባብዌ አንዷ ናት

ዶክተር ቴድሮስ የሙጋቤን ሹመት ባለፈው ሳምንት ያስተላለፉት የማይተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል በአቻዎቻቸው ላይ ተፅእኖ ማሳደር ይችላሉ በሚል ነበር።

የእንግሊዝና የካናዳ መንግስታትን ጨምሮ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ውግዘት ስለደረሰባቸውም ሹመቱን ቀልብሰውታል።

አራት አስርት ዓመታት ሊደፍን ትንሽ በቀራቸው አመራር የመጀመሪያዎቹ 20 ዓመታት ሙጋቤ የተሻለ የጤና ስርዓትን መዘርጋት ችለው ነበር።

ከዚምባብዌ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ጋር ተያይዞ የጤና ስርዓቱም ከፍተኛ ተፅእኖ ደርሶበታል።

የህክምና ባለሙያዎች ያለደሞዝ በሚሰሩበት፤ መድኃኒቶች በከፍተኛ ሁኔታ በሚያጥሩበት ሁኔታ በተቃራኒው ሙጋቤ ህክምናን ለመሻት ወደውጭ ይጓዛሉ።