ዳኞች ባለመሟላታቸው የኬንያ ፍርድ ቤት በምርጫው ላይ ሳይወስን ቀረ

ዋና ዳኛ ማራጋ Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ ዳኛ ዴቪድ ማራጋ

የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነገ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን የድጋሚ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔውን ለመስጠት ቀጠሮ ቢይዝም አስፈላጊው የዳኞች ቁጥር ባለመሟላታቸው ውሳኔ ሳይወሰጥ ቀረ።

ያለፈውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤትን ውድቅ ካደረጉት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች መካከል አንዱ የሆኑት ዋና ዳኛ ዴቪድ ማራጋ ናቸው ዳኞች ያለመሟላታቸውን ያሳወቅት።

ፍርድ ቤቱ ኬንያ ለምርጫ ዝግጁ አይደለችም በሚል ከሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች የቀረበለትን ጥያቄ ይመለከታል ተብሎ ነበር።

የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ጠበቃም ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ይካሄዳል ብለዋል።

የድጋሚ ምርጫውን ነገ ሐሙስ ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ቀደም ሲል የተካሄደውን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ውጤት መስከረም ላይ ውድቅ በማድረግ የድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ በማዘዝ ታሪካዊ የተባለ ውሳኔ አሳልፎ ነበር።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዋና ዳኛ ዴቪድ ማራጋ በወቅቱ እንዳሉት፤ ነሐሴ ላይ የተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሃገሪቱን ሕገ-መንግሥት መሰረት ባደረገ ሁኔታ ባለመካሄዱ ተቀባይነት የለውም ብለው ነበር።

ይህም በአፍሪካ በተካሄዱ ምርጫዎች ተቃዋሚ ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ የምርጫ ውጤትን ተቃውመው በፍርድ ቤት ሲረቱ የመጀመሪያው ነው።

ቢሆንም ግን የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ በድጋሚ ምርጫው ሂደት ላይ ጥያቄዎችን በማንሳት ከውድድሩ እራሳቸውን አግልለዋል።

ኦዲንጋ ትናንት ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሚካሄደው ምርጫ ''የኬንያዊያንን ፍላጎት የማይወክል የማስመሰል ድርጊት ነው'' ብለውታል።

ኦዲንጋ ጨምረው እንደተናገሩት ''ከመጀመሪያው ምርጫ በኋላ ምንም የተለወጠ ነገር የለም'' በማለት በምርጫው ቀን ''ግዙፍ'' ያሉትን ህዝባዊ ሰልፍ ጠርተዋል።