ፈር ቀዳጅ የታይፎይድ ክትባት ተገኘ

ክትባት በናይጀሪያ Image copyright Getty Images

ከአስር አይነት የታይፎይድ በሽታዎች ዘጠኙን መከላከል የሚያስችል አዲስ ክትባት በዓለም የጤና ድርጅት ቀርቧል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት በየዓመቱ ለ220 ሺህ ሰዎችን ሞት እንዲሁም ለ22 ሚሊዮን ሰዎች መታመም ምክንያት ለሆነው ለዚህ በሽታ መፍትሄ ይሆናል ብለዋል።

በዋናነት በበሽታው በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቁት ህፃናት ሲሆኑ፤ ይህ ክትባት ከሌሎች በተለየ ሁኔታም ህፃናት ላይ ውጤታማ ነው።

ክትባቱ በቀላሉ የሚዛመተውን የታይፎይድ በሽታን ለማጥፋት ይጠቅማልም ተብሎ ተስፋ ተደርጓል።

የታይፎይድ በሽታ የሚከሰተው ሳልሞኔላ ታይፊ በሚባል ባክቴሪያ ሲሆን ምልክቶቹም፡

  • ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ትኩሳት
  • የራስ ምታት
  • ማቅለሽለሽ
  • የምግብ ፍላጎት መቀነስ
  • የሆድ ድርቀት
  • ከመቶ ሰዎች መካከል አንዱን አስከሞት ሊያደርስ።

በተበከለ ምግብና ውሃ አማካኝነት የሚተላለፈው ይህ በሽታ ከፍተኛ የመተላለፍና የመሰራጨትም ባህርይ አለው።

የንፅህና ችግርና የንፁህ ውሃ አቅርቦት ችግር ያለባቸው አካባቢዎች በከፍተኛ ደረጃ ለበሽታው ተጋላጭ ሲሆን፤ የታይፎይድ በሽታ በደቡብ እስያ እንዲሁም ከሰሀራ በታች ባሉ ሃገራት በስፋት ይከሰታል።

በአሁኑ ጊዜ ይህን በሽታ ለመከላከል ሁለት የታይፎይድ ክትባቶች የፀደቁ ሲሆን፤ እስካሁን ከሁለት ዓመት በታች ላሉ ህፃናት ፍቃድ ያለው ክትባት አልነበረም።

በአለም አቀፍ ጤና ድርጅት የክትባቱን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተለው ቡድን መሪ ፕሮፌሰር አሌሃንድሮ ክራቪዮቶ "ለመጀመሪያ ጊዜ ውጤታማ የሆነ ክትባት አግኝተናል" ብለዋል።

ቡድኑም ክትባቱ ስድስት ወር ለሆናቸው ህፃናት ጭምር እንደሚሰጥ ገልጿል።

ፕሮፌሰር አሌሃንድሮ እንዳሉት በዓለማችን በተሰራጩት በርካታ አይነት ፀረ-ተህዋሲያን መድሃኒቶች ምክንያት የታእፎይድ ባክቴሪያ መድሃኒቶቹን እየተላመደ በመምጣቱ ምክንያት የዚህ ክትባት መገኘት ትልቅ እመርታ ነው ብለዋል።

ክትባቱ ላይ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ በተደረገ የክሊኒክ ሙከራ የተገኙ መረጃዎች በላንሴት የሜዲካል ጆርናል ላይ ታትሟል።

በጥናቱ 112 ሰዎችን ታይፎይድን በሚያስከትለው ባክቴሪያ እንዲያዙ ተደርጎ የክትባቱ ውጤታማነት የተሞከረ ሲሆን 87 በመቶ ተፈላጊውን ውጤት አስገኝቷል።

ሙከራውን ያደረጉት ፕሮፌሰር ፖላርድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግኝቱን "ፈር ቀዳጅም ነው" ብለዋል።