"አካል ጉዳተኝነት ህይወቴን በሌላ አቅጣጫ እንዳይና ሌላ የህይወት ምዕራፍ እንዲኖርኝ አደርጓል"

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

"አካል ጉዳተኝነት እንደፈተነኝ ይኖራል"

"አካል ጉዳተኛ ባልሆን ኖሮ እንኳን ይህን ዓለም አቀፍ ሽልማት ልወስድ አንደኛ ክፍልም አልማርም ነበር" የምትለዉ የትነበርሽ ንጉሴ ዘ ራይት ላይቭሊሁድ አዋርድን ካሸንፉ ጥቂት ሰዎች መካከል አንዷ ሆናለች።

"ዓይነ-ስዉር በመሆኔና ለእኔ የሚሆን ነገር በተወለድኩበት አከባቢ ባለመኖሩ እናቴ ትልቅ መስዋዕትነት ከፍላ ወደ ከተማ እንድመጣ አደረገችኝ" በማለት የማይረሳዉን የህይወቷን ጉዞ ታስታዉሳለች።

የ 35 ዓመቷ የትነበርሽ ንጉሴ፤ ዓይነ-ስዉርነቷ ገና በልጅነት እድሜዋ ነበር ከተወለደችበት ስፍራ ከ 800 ኪሎ ሜትሮች በላይ እንድትጓዝ ያደረጋት።

በለጋ የዕድሜዋ ያጋጠማት የዓይን ህመም በተደረገላት ህክምና አልድን አለ። ይህንን ተከትሎ የትነበርሽ ሻሸመኔ ካቶሊክ ዓይነ-ስዉራን ትምህርት ቤት ትምህርቷን እንድትከታተል ተደረገ።

ዓይነ-ስውር መሆኗ ትምህርት እንድታገኝ ከማድረጉ በተጨማሪ በተወለደችበት አካባቢ ልማድ የነበረዉን ያለዕድሜ ጋብቻ እንድታመልጥ አድርጓታል።

ስለዚህም "አካል ጉዳተኝነት ህይወቴን በሌላ አቅጣጫ እንዳይና ሌላ የህይወት ምዕራፍ እንዲኖርኝ አደርጓል" ትላለች የትነበርሽ ንጉሴ።

ብረተሰብ እና ህግ

ኢትዮጵያ ካላት ህዝብ መካከል 17.5 በመቶ የሚሆኑት ወይም 15 ሚሊዮን ሰዎች አካል ጉዳተኞች እንደሆኑ የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

ይህ አሃዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው 15 በመቶ ጋር ሲነጻጸር በ 2.5 በመቶ ከፍ ያለ ነው።

የምስሉ መግለጫ,

"አካል ጉዳተኛ መሆኔ ጥሩ ደረጃ እንድደርስ አድርጎኛል" የትነበርሽ ንጉሴ

በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለ የግንዛቤ እጥረት፣ የአካል ጉዳተኞች መብት ያለመከበር፣ አብዛኛዎቹ መሠረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን ያገናዘቡ ያለመሆናችዉና ሌሎች መሰል ጉዳዮች ደግሞ በአገሪቱ ዉስጥ ያሉ የአካል ጉዳተኞችን ህይወት ፈታኝ የሚያደርጉ ናችዉ።

የአካል ጉዳተኞችን ክብር የሚነኩና መስተካከል ያለባቸዉ ቃላት በተለያዩ ሀገር አቀፍ ሰነዶች ዉስጥ እንዳሉና መስተካከል እንዳለባችዉ የምትናገረዉ የትነበርሽ ንጉሴ የፍትሀ ብሄር ህግ አንቀጽ 339 እና 340'ን እንደምሳሌ ታነሳለች።

በኅብረተሰቡ በኩልም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች ቢኖሩም የሚታዩት የአመለካከት እና የግንዛቤ ችግሮች ቀላል እንዳልሆኑ ትናገራለች።

"አካል ጉዳተኝነት እንደፈተነኝ ይኖራል"

ኢትዮጵያ ዉስጥ ሴት መሆን በራሱ ብዙ ፈተናዎች ያሉት ጉዳይ ነዉ ትላለች የትነበርሽ።

የጾታ እኩልነት ግንዛቤ በደንብ ባልተስፋፋባት ሀገር ሴት አካል ጉዳተኛ መሆን ደግሞ ፈተናዉን ከባድ የሚያደርገው መሆኑን ትናገራለች።

"ይህ አመለካከት እየተሻሻለ መሆኑን መካድ ባልፈልግም፤ አሁንም ሴቶች እንደ ጠባቂ ነዉ የሚታዩት። አካል ጉዳተኛ ደግሞ እንደ እርዳታ ፈላጊ ነዉ የሚታየዉ። እነዚህ ሁለቱ ተደምረዉ የስኬታችን መንገድ ሩቅ እንዲሆን ያደርጋሉ።"

"ሴትነት እና አካል ጉዳተኛነት የየራሳቸዉን ፈተና ይዘዉ ነዉ የሚመጡት" የምትለዉ የትነበርሽ ንጉሴ፤ "በሴቶች እኩልነት የሚያምን ህብረተሰብ ዉስጥ ብንሆን እንኳን አካል ጉዳተኛነት ራሱን የቻለ ፈተና ይሆንብናል" ትላለች።

ለእናቷና ለአያቷ ትልቅ አክብሮት እንዳላት እና ለአሁኑ ስኬቷ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸዉ የምታምነዉ የትነበርሽ፤ በሴትነቷ ብዙም ፈተና እንዳልገጠማት ገልጻ አካል ጉዳተኝነት ግን አሁንም እንደሚፈትናት ትናገራለች።

"ቀነኒሳ እና ኃይሌ ሲያሸንፉ ከንፈር አንመጥም። አካል ጉዳተኛ ሆነህ ስኬታማ ስትሆን ግን ከንፈር ይመጠጥልሃል። ነገር ግን ያሰዉ አካል ጉዳተኛ ከመሆኑ ባሻገር ብዙ የሚችለዉ ነገር ስላለ እንዳየነዉ ከንፈር ባንመጥ ጥሩ ነዉ" ትላለች የዚህ ዓመት የአማራጭ ኖቤል ሽልማት አሸናፊዋ ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ።

የግንዛቤ እጥረት የተለመደ ምክንያት

"አብረዉ ተጫዉተዉ ያደጉ ህጻናት ነገ አብሮ መስራት፣ መጋባት እንዲሁም አብረዉ ሃገር መለወጥ ይችላሉ" የምትለዉ የትነበርሽ፤ ሌሎች ትምህርት ቤቶች አልቀበል ያሏቸዉን አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በራሷ ትምህርት ቤት ተቀብላ ታስተምራለች።

"ትምህርት ቤት የተሻለ ነገር ለመፍጠር እንጂ የነበረዉን ለመድገም መቋቋም የለበትም" ትላለች።

አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተቀላቅለዉ እንዲማሩ በማድረግም ስለአካል ጉዳተኞች የተሻለ ግንዛቤ እና አመለካከት ያለዉ ትዉልድ መፍጠር እንደሚቻልም የትነበርሽ ትናገራለች።

አንዴም ሆነ በተደጋጋሚ ለሚፈጠሩ ማህበራዊ ችግሮች የግንዛቤ እጥረት እንደ ምክንያት ይነሳል።

አካል ጉዳተኞች ላይ ለሚደርሱ መገለልን ጨምሮ ሌሎች የአመለካከት ችግሮች የግንዛቤ እጥረት ፈጣኑና የመጀመሪያዉ ምክንያት ሲሆን ይታያል።

"ስለ አካል ጉዳተኞች መብት ስላነሳን ችግሩ አይፈታም" የምትለዉ የአካል ጉዳተኞችና የሴቶች መብት ተከራካሪ የሆነችው የትነበርሽ ንጉሴ ሁልጊዜ የሁሉም ሰዉ እኩልነት መብት እንዳይጣስ መስመር ማበጀት እንደሚያስፈልግ ትናገራለች።

"በተጨማሪም ትምህርትቤቶች፣ የህግ እና የመገናኛ ብዙሃን አካላት የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስጠበቅ እና እኩልነታቸዉን ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና አላቸዉ" ትላለች።