የታይላንዱ ንጉሥ ከሞቱ አንድ ዓመት በኋላ ግብዓተ መሬታቸው ተፈፀመ

14ሺህ ኪሎግራም የሚመዝነውና የንጉሱን አስከሬን የያዘው ጋሪ በ200 ወታደሮች ታጅቦ ግብዓተ መሬት ወደሚፈፀምበት ሥፍራ እየተጓዘ ይገኛል። Image copyright AFP

ንጉሥ ቡሚቦል ኣዱልያዴጅ ባለፈው ዓመት ወርሃ ጥቅምት ላይ ነበር ይህችን ዓለም በሞት የተለዩት።

በቡድሂስት መነከኮሳት እና በታዳሚዎች ታጅቦ ወደቀብር ሥፍራ የመጣው የንጉሱ አስከሬን በቡድሂዝም እምነት መሠረት በሥርዓቱ ፍፃሜ ላይ ይቃጠላል።

የንጉሱን አስከሬን የሚያቃጥሉት ልጃቸው ንጉስ ማሃ ቪጂራሎንግኮርን ናቸው።

የአምስቱ ቀናቱ ሥነ-ሥርዓት ዕለተ-ረቡዕ በይፋ የተጀመረ ሲሆን ዋና ከተማዋ ባንኮክ በቢጫና ወርቃማ ቀለሞች አጊጣለች።

14 ሺህ ኪሎግራም የሚመዝነውና የንጉሡን አስከሬን የያዘው ጋሪ በ200 ወታደሮች ታጅቦ የመጨረሻው ሥነ-ሥርዓት ወደሚፈፀምበት ሥፍራ እየተጓዘ ይገኛል።

ወደ 250 ሺህ ታይላንዳዊያን እንደሚሳተፉበት የተገመተው ይህ ሥነ-ሥርዓት ከሌሎች አርባ ያህል ሃገራት የሚመጡ እንግዶች እንደሚሳተፉበትም ታውቋል።

ንጉሡ የአባታቸውን አስከሬን ካቃጠሉ በኋላ ዕለተ-አርብ አመዳቸው ተመልሶ ወደ ቤተ-መንግስት ይገባል። ከዚያም ለሁለት ተጨማሪ ቀናት ሥርዓቱ ይቀጥላል።

Image copyright AFP

ሟቹ ንጉሥ በታይላንዳውያን ዘንድ ተወዳጅ እንደነበሩና የሃገሪቱን ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን በማረጋጋት ወደሰከነ መንፈስ እንዳመጡ ይነገራል።

ንጉሥ ቡሚቦል አዱልያዴጅ ባለፈው ዓመት ወርሃ ጥቅምት ላይ ከሞቱ ጀምሮ ታይላንድ ለአንድ ዓመት ያክል ሃዘን ላይ የነበረች ሲሆን ሰዎች ጥቁር ለብሰው ይታዩም ነበር።

አናብስትና ዝሆኖችን የመሳሰሉ እንስሳትና እና በተለያዩ ዓይነቶች የተሠሩ ቅርፃ ቅርፆች በቀብር ሥፍራው እንደሚገኙም ታውቀል።

ሥነ-ሥርዓቱን የሚታደሙ ጎብኚዎች ጥቁር እንዲለብሱ ባይገደዱም በወጉ ለብሰው እንዲመጡ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።

በታይላንድ የንጉሡን ቤተሰቦች ያልተገባ ነገር መናገርና መሳደብ ለከፍተኛ ቅጣት የሚዳርግ ጥፋት ነው፤ ይህም ከሌሎች ንጉሣዊ ሃገራት ለየት ያደርጋታል።

ተያያዥ ርዕሶች