በጥብቅ ጥበቃ ስር ኬንያ ምርጫ እያካሄደች ነው

የኬንያ ምርጫ

ለሁለተኛ ጊዜ ለመመረጥ የሚወዳደሩት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ዜጎች ድምፅ እንዲሰጡ እና ስላም እንዲጠበቅ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ራይላ ኦዲንጋ ድጋፊዎቻቸው በምርጫው እንዳይሳተፉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ተካሂዶ የነበረውን ምርጫ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ቢያሽንፉም ራይላ ኦዲንጋ ለሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረቡት አቤቱታ የምርጫው አካሄድ 'መዛባት' ታይቶበታል በሚል ውጤቱ መሰረዙ ይታወሳል።

ዛሬ እየተካሄደ ባለው ዳግም ምርጫ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ክፍት ሆነው መራጮችን እያስተናገዱ ነው። ነገር ግን የድምፅ ሰጪዎች ቁጥር ቀደም ሲል ከተደረገው ምርጫ አንፃር ዝቅተኛ እንደሆነ እየተነገረ ነው።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የፀጥታ ጥበቃ ኃይሎች የመራጮችን እና የምርጫ ጣቢያዎችን ደህንነት ለመጠበቅ በመላው ሃገሪቱ ተሰማርተዋል ተብሏል።

Image copyright Andrew Renneisen
አጭር የምስል መግለጫ ነሃሴ 2 የተካሄደው ምርጫ

በምርጫው ዋዜማ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ባስተላለፉት መልዕክት 'አባቶቻችን የመምረጥ እድል እንደናገኝ መስዋትነት ከፍለዋል፤ ይህን እድል በአግባቡ መጠቀም ይኖርብናል' ሲሉ ዜጎች ድምፅ እንዲሰጡ አሳሰበዋል።

የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ አሸንፈዋል ብሎ አውጆ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የምርጫውን ውጤት ውድቅ ካደረገ በኋላ በኮሚሽኑ ላይ ከፍተኛ ወቀሳዎች እና ጥቃቶች ሲፈፀሙ ቆይቷል።

ባሳለፈነው ሳምንት የምርጫ ኮሚሽኑ ከፍተኛ ሃላፊ የግድያ ማስፈራሪያ ከደረሳቸው በኋላ ወደ አሜሪካ ሸሽተዋል።

ከመጀመሪያው ምርጫ እሰካሁን ድረስ ባሉት ሦስት ወራት ውስጥ ከምርጫ ጋር ተያይዞ በተከሰቱ ግጭቶች ከሰባ በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ፖሊስ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ ሲተኩስ።

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ራይላ ኦዲንጋ የድጋሚ ምርጫው ወደፊት እንዲካሄድ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ቢጠይቁም ዳኞች ሳይሟሉ በመቅረታቸው ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሳይሰጥ ቀርቷል።

ከነሐሴው ምርጫ በኋላ ውዝግቡ ወደፍርድ ቤት ሄዶ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዋና ዳኛ ዴቪድ ማራጋ 'ምርጫው በህገ-መንግሥቱ መሰረት አልተካሄደም' ስለዚህም የምርጫው ውጤት 'ልክ ያልሆነ እና ወጋ ቢስ' ነው በማለት ውድቅ አድረገዋል።

ዋና ዳኛው እንዳሉት ከስድስቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዳኞች አራቱ የምርጫ ኮሚሽኑ ውጤቱን ሲያስተላልፍ መዛባት ተፈፅሟል ብለዋል ።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ የምርጫው ውጤት 'ግልፅ አልነበረም ሊረጋገጥም አይችልም' ብሎ ነበር።

ራይላ ኦዲንጋ የምርጫ ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት የፈፀመውን አይነት ስህተት እንዳይደገም ምንም አይነት ማሻሻያ አላደረገም ቢለው ቢከሱም ኮሚሽኑ ይህን ክስ ውድቅ ያደርጋል።

ጥምር የፖለቲካ ፓርቲያቸው ምርጫው ላይ የሚሳተፈው የምርጫ ኮሚሽኑ አስፈላጊውን ማሻሻያ ሲያደርግ እንደሆነ ቀድመው አሳውቀው ነበር።

ኦዲንጋ ዛሬ እየተካሄደ ያለውን ምርጫ ለማጨናገፍ 'ግዙፍ' ህዝባዊ ሰልፍ እደሚጠሩ አሳውቀው፤ አስከፊ ግጭት እንዳይከሰት ደጋፊዎቻቸው በምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ እንዳይገኙ ጠይቀዋል።