ድጋሚ ምርጫው ኬንያዊያንን ለሁለት ከፍሏል

የኬንያ ምርጫ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በአንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለመምረጥ ወጥተዋል

ኬንያውያን ውዝግብ ባልተለየው ዳግም ምርጫ መሪያቸውን ሲመርጡ ውለዋል።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምር ናሳ አልሳተፍበትም ባለው የድጋሚ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ኬንያውያን በከፍተኛ የፀጥቃ ጥበቃ ስር ሆነው ነበር ድምፅ እየሰጡ የዋሉት።

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎች በሚበዙበት አካባቢ የድምፅ ቁጥር አነስተኛ የነበረ ሲሆን በኪሱሙ የምርጫ ክልል ደግሞ የምርጫ ጣቢያዎች ሳይከፈቱ ውለዋል።

በሌላ በኩል ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ድምፃቸውን ከሰጡ በኋላ ዜጎች ወጥተው መሪያቸውን እንዲመርጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎች ባሉባቸው አካባቢዎች የመራጮች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ተስተውሏል።

በናይሮቢ ከተማ በኪቤራ አካባቢ፣ በሞምባሳ እና በኪሱሙ የራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።

አጭር የምስል መግለጫ ተቃዋሚዎች በጠሩት በምርጫ ያለመሳተፍ ምክንያት አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች መራጭ አልነበራቸውም

የኬንያ የምርጫ ኮሚሽን ነሃሴ 8 ተካሂዶ በነበረው ምርጫ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ አሸንፈዋል ብሎ ቢያውጅም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የምርጫውን ውጤት ውድቅ ካደረገ በኋላ በኮሚሽኑ ላይ ከፍተኛ ወቀሳዎች እና ጥቃቶች ሲፈፀሙበት ቆይቷል።

ራይላ ኦዲንጋም ኮሚሽኑ ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ አስፈላጊውን ማሻሻያዎች አላደረገም በማለት የድጋሚ ምርጫው ወደፊት እንዲካሄድ ጠይቀው ነበር።

የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምርጫውን እንዲያራዝም ቢጠየቅም ዳኞች ሳይሟሉ በመቅረታቸው ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሳይሰጥ ቀርቷል።

በፀጥታ ምክንያት ምርጫ ያልተካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች በመጪው ቅዳሜ ምርጫው እንደሚካሄድ ኮሚሽኑ ገልጿል።