የናይጀሪያ ህፃናት የኩፍኝ ወረርሽኝ አደጋ ላይ ናቸው

ክትባት በናይጀሪያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኩፍኝ በከፍተኛ ሁኔታ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን፤ በቀላሉም በክትባት በሽታውን መከላከል ይቻላል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ካልተከተቡት 20 ሚሊዮን ህፃናት መካከል 3 ሚሊዮኑ ናይጀሪያ ውስጥ እንደሚገኙ አዲስ የወጣ ሪፖርት ያሳያል።

ሁለቱ አፍሪካውያን ሀገሮች ኢትዮጵያና ኮንጎም ከሌሎች በተለየ መልኩ ቁጥራቸው ከፍ ያለ ያልተከተቡ ህፃናት ልጆች ያሉባቸው ሀገራት እንደሆኑ ሪፖርቱ ጨምሮ ያስረዳል።

ይህ ሪፖርት የወጣው ዝናብ በማይዘንብበት በበጋ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞች ስጋት በሆኑበት ወቅት ነው።

በናይጀሪያ ከኅዳር እስከ መጋቢት ባለው ወቅት የከፋ የኩፍኝ ወረረሽኝ የሚከሰትበት ጊዜ ነው።

በባለፈው ዓመት ከጥር እስከ መስከረም ባለው ወቅት በሰሜን ምሥራቅ ናይጀሪያ አካባቢ 3 ሺህ ያህል የሚሆኑ በኩፍኝ የተጠረጠሩ ህሙማን እንዳሉ ሪፖርት ተደርጓል።

በዚሁ አካባቢ አሁንም ባሉት ግጭቶች የተነሳ የጤና ተቋማት ከአገልግሎት ውጭ ሲሆኑ፤ ሰባት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችም የጤና ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል።

ይህ ሪፖርት እንደ ዓለም ጤና ድርጅት፣ የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው በጥምረት ያወጡት ሲሆን፤ ከዚህ በኋላም ከፍተኛ የሆነ ወረርሽኝ ሊከሰት እንደሚችል ጠቁሞ። በሽታው ውስብስብ ለሆኑት የሳንባ ምች፣ ዓይነ-ስውርነት እንዲሁም ለሞት እንደሚዳርግ ይገልፃል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ለግጭት በተጋለጡ አካባቢዎች ላይ በቆየ የሁለት ሳምንት የክትባት ዘመቻ፤ ዕድሜያቸው ከአስር ወራት እስከ አስር ዓመት የሆኑ አራት ሚሊዮን ልጆች ተከትበዋል።