የአስመራው ት/ቤት ኣገልግሎት መስጠት ጀመረ

ኤርትራዊያን ሕፃናት

ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 20 ቀን 2010 በአስመራ ከተማ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ በሰው ሕይወት ላይ አደጋ ባይደርስም በርካታ ወጣቶች ለእስር እየተዳረጉ እንደሚገኙ ታውቋል።

ወጣቶቹ የታሰሩት አስመራ በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች ሲሆን ተቃውሞውን ተከትሎ ለእስር ከተዳረጉት መካከል ለአቅመ ኣዳም ያልደረሱ ታዳጊዎች መፈታታቸውን በአካባቢው የሚገኙ ምንጮቻችን ገልፀዋል።

አኽርያ በመባል የሚታወቀውን አካባቢ ሲጠብቁ የነበሩ የፀጥታ ኃይሎችም አካባቢውን ለቀው የወጡ ሲሆን፤ ለተቃውሞው መነሻ የሆነው የአልድያዕ አል ኢስላምያ ትምህርት ቤት ስራውን መጀመሩንና ተማሪዎችም ወደ መደበኛ ትምህርታቸው መመለሳቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ምንጮቻችን እንደገለፁልን ልጆቻቸው የታሰሩባቸው ወላጆች ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ የልጆቻቸውን ሁኔታ ሲጠይቁና ምግብ ሲያመላልሱ ተስተውለዋል።

የኤርትራ ማስታወቅያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገ/መስቀል በተቃውሞው ምንም ዓይነት የሰው ሕይወት እንዳልጠፋ በትዊተር ገፃቸው ፅፈዋል።

በአስመራ የጣልያን ኢምባሲ ሠራተኛ የሆኑት ዲዬጎ ሶሊናስ በበኩላቸው በገጠመው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የተጎዳ ሰው እንደሌለ መታዘባቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የትምህርት ቤቱ ባለቤትነት ዝውውርን በመቃወም የተማሪ ወላጆች በተሰበሰቡበት ንግግር በማደረጋቸው ለእስር የተዳረጉት ሓጂ ሙሳ መሓመድን እና ሌሎች ሰዎች ደህንነታቸውና ያሉበት ሁኔታ እስካሁን እንደማይታወቅ ምንጮቹ ጨምረው ገልፀዋል።