ትምህርት ዕድሜን እንደሚያስረዝም በጥናት ተረጋገጠ

ትምህርት

ሰዎች በትምህርት ላይ የሚያሳልፉት እያንዳንዱ ዓመት በእድሜያቸው ላይ በአማካይ 11 ወራትን እንደሚጨምር ሳይንቲስቶች አረጋገጡ።

እድሜን ከሚያራዝሙ ነገሮች በተጨማሪ የሚያሳጥሩ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉም አመልክተዋል።

አጥኚዎቹ እንደሚሉት አንድ ሰው ከልክ በላይ በሚጨምረው በእያንዳንዱ ኪሎ ግራም ከእድሜው ላይ ሁለት ወርን ሲቀንስ በቀን አንድ ፓኮ ሲጋራ የሚያጨስ ሰው ደግሞ ከዕድሜው ላይ ሰባት ዓመታትን ያሳጥራል።

የኤደንብራ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን እዚህ ውጤት ላይ የደረሰው ባልተለመደ ሁኔታ የሰዎችን የዘረ-መላዊ መለያዎችንና የዘር ቅንጣቶችን ልዩነት በመተንተን ነው።

ተመራማሪዎቹ እንደሚያስቡት ውጤቱ ሰዎች ረጅም ዕድሜን እንዲኖሩ የሚያስችል አዲስ መንገድን ለማወቅ ያስችላል ብለዋል።

የአጥኚዎቹ ቡድን ግዙፍ በሆነው ተፈጥሯዊ የጥናት ሙከራ ላይ የተሳተፉ ከ600 ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን ዘረ-መላዊ መለያዎችን ተጠቅመዋል።

አንድ ሰው በተመሳሳይ የሚያጨስ፣ የሚጠጣ፣ ትምህርቱን ያቋረጠ ከሆነና ከልክ ያለፈ ክብደት ካለው፤ ጤናማ ያልሆነውን የአንዱን ነገር ተፅዕኖ ለይቶ ለማወቅ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።

ከዚህ ይልቅ አጥኚዎቹ ተፈጥሯዊ ወደሆነው ሙከራ ፊታቸውን መልሰዋል።

አንዳንድ ሰዎች በዘር ቅንጣታቸው ውስጥ ምግብን አብዝተው እንዲመገቡ የሚያደርግ ወይም ለውፍረት የሚያጋልጥ ተፈጥሮ ሊኖራቸው ይችላል።

ስለዚህም አጥኚዎቹ አብዝተውና በልኩ የሚመገቡ ሰዎችን ተጨማሪ የሕይወት ዘይቤዎችን ሳያካትት ለማነፃፀር ችለዋል።

Image copyright Getty Images

ዶክትር ፒተር ጆሺ እንደሚሉት ''ክብደት መጨመር በቀጥታ በዕድሜ ላይ የሚያስከትለውን ውጤት በተመለከተ ለማወቅ ይቻላል። ይህም ትንተናውን አያፋልሰውም'' ብለዋል።

ተመሳሳይ የተፈጥሮ ይዘቶችም ሰዎች በትምህርት ላይ የሚያሳልፉትን ዓመታትና በማጨስ ወይም በመጠጣት ከሚያገኙት እርካታ ጋር እንዲያያዙ ተደርገዋል።

የጥናት ቡድኑ በተጨማሪም በዘር ቅንጣቶች ውስጥ ዕድሜ ላይ ተፅዕኖ ያላቸው የተለዩ ይዘቶችን ማግኘታቸውን ሳይንሳዊ ጥናት በሚቀርብበት መጽሔት ላይ አስፍረዋል።

  • የተፈጥሮ በሽታን የመከላከል አቅማችንን የሚያንቀሳቅሱ በዘር ቅንጣቶች በእድሜያችን ላይ ሰባት ወራት ያህል ሊጨምሩ ይችላሉ።
  • በዘር ቅንጣት ላይ ለጤና ጠንቅ የሆነ ኮሌስትሮል እንዲጨምር የሚያደርጉ ለውጦች ሲኖሩ ደግሞ ከእድሜያችን ላይ ስምንት ወራትን ይቀንሳል።
  • ከእርጅና ጋር የሚመጣ አዕምሯዊና አካላዊ እክልን የሚያስከትለው ብዙም ያልተለመደ የዘር ቅንጣት ለውጥ ከዕድሜ ላይ 11 ወራትን ያሳጥራል።

ዶክተር ጆሺ እንደሚሉት እነዚህ የዘረ-መል ይዘቶች ላይ የሚታዩ ልዩነቶች ''በጣም ትንሽ ጉዳዮች ናቸው'' ብለዋል።

በእድሜ ላይ ለውጥን ከሚያስከትሉ ልዩነቶች ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት በዘር የሚመጡ ሊሆኑ ይችላሉ።

ነገር ግን አስካሁን ተለይተው የታወቁት 1 በመቶው ብቻ ናቸው።

ዶክተሩ እንደሚሉት ዘረ-መል በምንኖረው እድሜ ላይ ተፅዕኖ ያለው ቢሆንም ''እያንዳንዳችን በአኗኗር ዘይቤያችን ላይ በምናደርገው ምርጫ መሰረት የበለጠ ተፅዕኖ የማድረግ አቅም አለን'' ብለዋል።

ዶክተር ጆሺ ለቢቢሲ እንደገለፁት ''እድሜ ላይ ተፅዕኖ ያላቸውን ቀዳሚ የዘር ቅንጣቶችን በመለየት ስለእርጅናና መፍትሄው አዳዲስ መረጃዎችን እናገኛለን ብለን ተስፋ እንደርጋለን''ብለዋል።

ረጅም ዕድሜ እንዳንኖር የሚያደርጉ የበሽታ አይነቶችም እንዳሉ ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል።

ተያያዥ ርዕሶች