ከማደጎ ልጅነት ወደ እውቅ ገጣሚና የማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ሃላፊነት

Image copyright Aida Muluneh

ነጮቹ ለምን ሲሴ እይሉ ይጠሩታል። በ1950ዎቹ መጨረሻ ላይ ለትምህርት ወደ እንግሊዝ ሃገር የሄደችው የማርእሸት ያልፈቀደችውን ልጅ ታረግዛለች። ልጅ ወልዶ ለማሳደግ ዝግጁ ስላልነበረች የወለደችውን ልጅ 'ለምን' ብላ ሰየመችው። ከዚያም ለምን ሲሳይ በሁለት ወሩ ለማደጎ ተሰጠ።

ከወራት በኋላ የማርእሸት ልጇን ማሳደግ የምትችልበት ደረጃ ላይ ስትደርስ ልጄን መልሱ ብላ አቤቱታ አቀረበች። የማህበራዊ አገልግሎቱ ግን ፍቃደኛ ሳይሆን ቀረ።

ኖርማን የተባለው የማህበራዊ አገልግሎት ሰራተኛ ስሙን ከ 'ለምን' ወደ ራሱ ስም 'ኖርማን' ቀየረው። ከዚያም ለነጭ አሳዳጊዎች በማደጎነት ሰጠው።

ወግ አጥባቂ የነበሩት የማደጎ ወላጆቹ በሙያቸው መምህር እና ነርስ ነበሩ። ለምን የልጅነት ጊዜውን ''አስከፊ'' ሲል ይገልፀዋል። በእድሜ ከፍ እያለ ሲመጣ ለአሳዳጊዎቹ ''አስቸጋሪ'' ልጅ ሆነ።

ምግብ የመብላት ፍላጎት የለውም፣ ወደ ቤት መግባት አይፈልግም፣ በአጠቃላይ በህይወቱ ደስተኛ አልነበረም። 12 ዓመት ሲሞላው አሳዳጊዎቹ ዳግመኛ ልናየው ፍቃደኛ አይደለንም ብለው ለማህበራዊ አገልግሎት ሰራተኞች መልሰው ሰጡት።

አስራ ስምንት ዓመት እስኪሆነው ድረስ በአራት የህፃናት ማሳደጊያ ቤቶች ውስጥ ኖሯል። በእነዚያ ዓመታትም በዘር ላይ የተመሰረቱ አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃቶች ተፈፅመውበታል። ወላጅ እናቱም ጥላው እንደሄደች፤ ወገን እንደሌለው ይነገረው ነበር።

አስራ ስምንት ዓመት ከሆነው በኋላ ስለ እራሱ እና ወላጅ እናቱ የሚያትቱ ጥቂት መረጃዎች ተሰጥተውት ከማደጎ አንዲወጣ ተደረገ። በዚያን ወቅት ነበር ወላጅ እናቱ ''ለምን'' ብላ እንደሰየመችው እና የማህበራዊ አገልግሎት ሰራተኛው ሰሙን ወደ ኖርማን እንደቀየረ የተረዳው።

እናቱም ለማህበራዊ አገልግሎት ልጇ እንዲመለስላት በፃፈችው ደብዳቤ ''ለምንን እንዴት መልሼ ማግኘት እችላለሁ? ከራሱ ሰዎች ጋር እንዲሆን እፈልጋለሁ፤ አድልዎ እንዲፈፀምበት አልፈልግም'' ስትል እንደተማፀነች የተረዳው። ብዙም ሳይቆይ መጠሪያ ስሙን ከኖርማን ወደ ለምን አሰቀየረ።

ለምን ከማደጎ ቤት ከወጣ በኋላ የብቸኝነት ስሜት እጅጉን ይሰማው እንደነበር ይናገራል። ''በበዓላት ወቅት የቤተሰብ አባላት በአንድ ላይ ተሰብሰበው ሲያከብሩ እኔ ግን ብቸኛ ነበርኩ። ለዚያም ነው አሁን በተቻለኝ አቅም በማደጎ ቤት ውስጥ ያሉ ልጆችን በቤቴ ሰብስቤ በገና ዋዜማ እራት የምጋብዛቸው'' ሲል ይናገራል።

Image copyright benjireid.com
አጭር የምስል መግለጫ ለምን የልጅነት ጊዜውን ''አስከፊ'' ሲል ይገልፀዋል

ለምን ከማደጎ ቤት ከወጣ በኋላ ማንችስተር ከተማ በሚገኝ ማተሚያ ቤት ውስጥ የሥነ-ፀሑፍ ሥራውን እየሰራ ወላጅ እናቱን ማፈላለግ ጀመረ።

ወላጅ እናቱን ለበርካታ ዓመታት ካፈላለጋት በኋላ፤ 21 ዓመት ሲሆነው ጋምቢያ ውስጥ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እየሰራች የነበረችውን የማርእሸትን አገኛት።

ለምን ስለ ወላጅ እናቱ ሲናገር ''የእናቴ ፎቶግራፍ የተሰጠኝ ከተማረችበት ኮሌጅ ሲሆን፤ እናቴን ለመጀመሪያ ጊዜ ሳገኛት 21 ዓመቴ ነበር። ይህም እሷ አባቴን ያገኘችበት እድሜ ማለት ነው። እናቴ እና አባቴ ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እኔ በተፀነስኩበት ምሽት ነበር።'' የሚለው ለምን ''የማርእሸት ሲሳይ አስደናቂ ሴት ናት። ካወራን ከዓመት በላይ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ተገናኝተናል'' ሲል ያስታውሳል።

ዛሬ ላይ ለምን የበርካታ ተወዳጅ መፅህፍት፣ የተውኔት ድርሰቶች እና የግጥሞች ፀሃፊ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ሲሆን ከሁለት የእንግሊዝ ሃገር ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬቶችን ተቀብሏል።

  • ለምን እና ሥራዎቹ
የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ለምን ሲሳይ ''Gold from the stone''

ለምን ሲሳይ ስለ ስራዎቹ እና ስለ ግል ህይወቱ ለቢቢሲ አማርኛ ሲናገር ''ሁሌም ስለእራሴ ታሪክ እና በማደጎ ቤቶች ውስጥ ያደረኩትን ትግልና ድል መጻፍ ያስደስተኛል። ያለፈኩበትን መንገድ ለሌሎች ማሳየት እፈልጋለሁ። መናገር የምፈልገውን ታሪክ ደግሞ በሥነ-ፅሁፍ መግለፅ ይቀለኛል።''

''በግጥም ማለት የማይቻለውን ሁሉ ማለት ይቻላል። ከልጅነቴ ጀምሮ ግጥም ትንቢታዊ ሃይል እንዳለው ይሰማኛል። በማደጎ ቤት ውስጥ እያለሁ የሚሰሙኝን የሃዘን ስሜቶች በግጥም ነበር የምገልፃቸው'' በማለት ለምን ለግጥም ያለውን ጥልቅ ስሜት ይናገራል።

ለሥነ-ጽሑፍ ምን እንዳበረከትኩ አላውቅም። በሥነ-ጽሑፍ ሥራዎቼ ግን ሰዎችን አነቃቅቼ ከሆነ ግን ትልቅ ኩራት ይሰማኛል።

ለምን ከ15 ዓመት በፊት የፃፈው እጅግ የተወደደለት ''Something Dark'' የተባለው መጽሃፉ የህይወቱን ታሪክ የሚተርክ እንደሆነ ይናገራል። ''ይህንን መፅሃፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት መድረክ ላይ አንብቤዋለው በቢቢሲ ሬዲዮም ተተርኳል'' ሲል ያስታውሳል።

  • ኢትዮጵያ እና ለምን

''እራሴን እንግሊዛዊ እና ኢትዮጵያዊ አድርጌ ነው የማስበው። ለኢትዮጵያ ጥልቅ ፍቅር አለኝ'' የሚለው ለምን፤ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ሥራዎቹን በተለያዩ መድረኮች እንዳቀረበ ይናገራል።

''ብዙ የሥነ-ጽሑፍ ስራዎቼ ወደ አማርኛ እንዲተረጎሙ ከኢትዮጵያውያን ጓደኞቼ ጋር እየተነጋገርኩ ነው። እዚህም በቅርብ የምጀመረው የነፃ የትምህርት እድል ፕሮግራም አለ። ይህ ፕሮግራም ኢትዮጵያዊ የሆኑ ተማሪዎችን በተለየ መልኩ ተጠቃሚ የደርጋል በዚህም ከፍተኛ ኩራት ይሰማኛል'' ይላል።

''በእንግሊዝ ሀገር ተወልጄ እንደማደጌ አማርኛ መናገር አልችልም'' አልችልም የሚለው ለምን ''Gold from the Stone'' የተባለው ሌላኛው መፅሃፉ በአሁን ጊዜ ወደ አማርኛ እየተተረጎመ እነደሆነ ተናግሯል።

ከሥነ-ጽሑፍ ሥራዎቹ በተጨማሪም ለምን በአሁን ወቅት የማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ሆኖ እየሰራ ይገኛል። ''እንደ ቻንስለርነቴ የዩኒቨርሲቲውን የቦርድ ስበሰባዎች እመራለሁ፤ እንዲሁም ተማሪዎችን አስመርቃለው። ቻንስለር ሆኜ ከተመረጥኩባቸው ምክንያቶች አንዱ የህግ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት እድል እንዲያገኙ በማደርገው ሥራ ነው'' ይላል።