ስሜታዊ ድራማ እና ትርዒት በሙምባይ ባቡር ጣቢያዎች ውስጥ

Mumbai commuters

23 ተሣፋሪዎች ሕንድ ሙምባይ ውስጥ በሚገኝ አንድ የባቡር ጣቢያ ውስጥ በተከሰተ ግርግር ተረጋግተው ከሞቱ እነሆ አንድ ወር ደፈነ። የቢቢሲዋ ኪንጃል ፓንድያ ዋግ በሙምባይ ባቡሮች ለአስር ዓመት ያህል ተመላልሳለች። እነሆ በኪናጃል የተሳናደውና በሙምባይ ባቡር ጣቢያዎች ውስጥ ምን እየተካሄደ እንዳለ የሚያትተው ፅሑፍ።

የሙምባይ ባቡሮች የከተማዋ እስትንፋስ ናቸው። በቀን ቢያንስ 8 ሚሊዮን ሰዎች ይመላለስባቸዋል። ሙምባይን ከባቡሮቹ በፊት እንዴት ትንቀሳቀስ እንደነበረ ማሰብ በራሱ ይከብዳል።

በዘጋቢ ፊልሞች፣ በማስታወቂያዎች እንዲሁም በቦሊውድ ፊልሞች ውስጥ የሙምባይ ባቡሮችን ማየት እጅግ የተለመደ ነው።

ባቡሮቹን መጠቀም ግን ሌላ ዓለም ነው፤ በሰው ብዛት የሚከሰተው መጨናነቅ ግን ከቁብም ላይቆጠር ይችላል።

የሙምባይ ከተማ ባቡሮችን መጠቀም ስጀምር ገና የኮሌጅ ተማሪ ነበርኩ። ወደ ትምህርት ቤቴ ለመሄድ የሁለት ሰዓት የባቡር ጉዞ ይጠይቃል።

አሁንም ሽታው፣ ግርግሩ ይታወሰኛል። በተለይ ደግሞ ባቡሩ ደቡብ ሙምባይ ባለው ፌርማታ ሲደርስ፤ እጅግ ደስ ይል ነበር።

ተጠቃሚዎች ስልካቸው ላይ ተጥደው ከሚታዩበት የሌላው ዓለም የከተማ ባቡር ሕይወት በተለየ የሙምባይ ባቡር ተጠቃሚዎች እርስ በርስ እየተጫወቱ ነው የሚጓዙት። ምንም ውይይት ሳያካሂዱ ዓይን ለዓይን እየተያዩ የሚመላለሱም እንዳሉ ሆነው።

በቡድን ሆነው የቦሊውድ ሙዚቃቸውን እየዘፈኑ የሚጓዙ ሰዎችን መመልከትም የተለመደ ነገር ነው።

ለሴቶች ብቻ ተብሎ በተከለለው ክፍል ደግሞ ልደት የሚያከብሩ እና ኬክ የሚያድሉ ብዙ ጊዜ ይስተዋላሉ።

ሃሜት የተለመደ ነገር ነው፤ የሥራ ቦታ ፖለቲካም እንዲሁ።

በሃያዎቹ መጨረሻ ላይ የምትገኛ አንዲት ሴት ስለ ዘመናዊቷ የሕንድ ሴት የኑሮ ውጣ ውረድ ምን የመሰለ ትንታኔ እየሰጠች ስትጓዝ የነበረች ሴት ዛሬም ትዝ ትለኛለች።

ደንገተኛ ብስጭት

በሙባይ ባቡሮች ውስጥ መቀመጫ ማግኘት እጅግ አዳጋች ነው፤ በተለይ ደግሞ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት።

ብዙ ጊዜ በተሳፋሪዎች መካከል ግጭት የሚነሳው በወንበር ምክንያት ነው። አንዳንዱ ግጭት ቶሎ ይቋጫል፤ ሌላው ደግሞ ከብዙ ንትርክ እና አንዳንዴም ከድብድብ በኋላ።

ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ቀድሜያቸው ስገባ ሊቀድሙን የሞከሩ ሰዎች ቲሸርቴን ቀደውብኛል። በተለይ ደግሞ ወንበር ለማግኘት የሚሯሯጡ ተጓዦች ብዙ ጉልበት ይጠቀማሉ።

የሙምባይ ባቡሮች በጣም አስፈሪው ነገር በሮቹ ባቡሩ ካልተንቀሳቀሰ በቀር አለመዘጋታቸው ነው።

ሌላው ደግሞ ባቡሩ ከመቆሙ በፊት ሮጦ ወደውስጥ መግባት ወንበር ስለሚያስገኝ ጊዜ ጠብቆ ዘሎ መግባት የግድ ነው።

እኔም ብዙ ጊዜ ባቡሩ ሲመጣ ዘልዬ ገባና ወይ የባቡሩን ብረት እይዛለሁ ወይም ደግሞ ቀድሞኝ የገባ ሰውን እጅ። እድል ከቀናኝ ወንበር አገኛለሁ፤ ካልሆነም ለሁለት ሰዓት ያህል ቆሞ መሄድ ግድ ይላል።

ቀድሞ መቀመጫ ያገኘ ሰውን መውረጃ ቦታ ጠይቆ መተካካትም ሌላው መላ ነው።

የሙምባይ ባቡሮችን መጠቀም እጅግ አዳጋች ሊሆን ይችላል። እጅግ ቀላል ሊሆንም ይችላል። ዋናው ነገር ስለባቡሩ ያለዎትን አመለካከት ማስተካከል ይጠይቃል።

ታጋሽና ሁሉ ነገር ቻይ እንድሆን አስተምሮኛል። የሙምባይ ባቡሮች ከተለያየ ዓለም የመጡ ሰዎች አንድ ላይ የሚሰበሰቡበት ሥፍራ ነው። ሁሉም ወደየመዳረሻው ለመሄድ የሚጠቀምባቸው መጓጓዣዎች።