የታገቱ ማስታወሻ ደብተሮች

ናዖሚ "ለማስታወሻ ነው የጻፍኩት"

ባለፈው ግንቦት ከቦኮ ሃራም እገታ ከተለቀቁት ልጃገረዶች መካከል አንደኛዋ ለጋዜጠኛ አዳዎቢ ትሪሻ ንዋኡባኒ ለሶስት ዓመታት በታሰረችበት ወቅት ስላስቀመጠችው የማስታወሻ ደብተር አጫውታታለች።

የ24 ዓመቷ ናዖሚ አዳሙ አብረዋት ይማሩ ከነበሩት መካከል በእድሜ ትልቋ ነበረች።

እ.አ.አ በ2014 እርሷን ጨምሮ በአብዛኛው ክርስቲያን የነበሩ ከ200 በላይ ሴት ተማሪዎች ታግተው በሰሜን ናይጄሪያ ወደሚገኘው ሳምቢሳ የተሰኘ የቦኮ ሃራም መደበቂያ ደን ተወሰዱ።

በእስር በነበሩበት ጊዜ ሴቶቹ ቁርዓን እንዲቀሩ ይደረግ ስለነበር ማስታወሻ የሚይዙበት ደብተር ተሰጥቷቸው ነበር።

ከመካከላቸው ግን አንዳንዶቹ ሴቶች የእገታውን ማስታወሻ ለመያዝ ተጠቀሙባቸው። ታጣቂዎቹ ባገኟቸውም ጊዜ ደብተሮቹን አቃጠሉባቸው።

ናዖሚ ግን የራሷን መደበቅ ችላለች። አሁን 20 የሞላት የቅርብ ጓደኛዋ ሳራ ሳሙኤልና ሶስት ሌሎች ልጃገረዶችም እነዚህን ደብተሮች ገጠመኞቻቸውን ለመመዝገብ ተጠቀሙባቸው።

የምስሉ መግለጫ,

ለማስታወሻ የተጠቀሙበት 2 ባለ 40 ገጽ ደብተሮች ተርፈዋል

የተገኙትም ማስታወሻዎች በመለስተኛ እንግሊዘኛና በደካማ ሃውሳ የተጻፉ ሲሆኑ ያለ ቀናት የተመዘገቡ ቢሆንም በታገቱባቸው የመጀመሪያ ወራት አካባቢ የተጻፉ መሆናቸው ግልጽ ነው።

ለማገት አላሰቡም ነበር

በአውሮፓውያኑ ሚያዚያ 14, 2014 ዓ.ም የቺቦክ ትምህርት ቤት ላይ ጥቃት ያደረሱት ታጣቂዎች አመጣጣቸው ሞተር ለመስረቅ እንጂ ልጃገረዶቹን ለማገት አልነበረም ።

የፈለጉትም ሞተር የትኛው እንደነበር ግልጽ ባይሆንም የመኪና ይሁን ሌላ ለማወቅ አዳጋች ሆኗል።

ሆኖም በአካባቢው የግንባታ ሥራ እየተካሄደ ስለነበረ ድንገት ሲሚንቶ የሚያቦካውን ሞተር ፈልገው ሊሆን ይችላል፤ ይህም ሞተር ደረቅ መሣሪያዎችን ለመሥራት መጠቀም ስለሚቻል ሊሆን ይችላል።

ሞተሩን በአካባቢው ማግኘት ሲያቅታቸው ግን ሰብሰበዋቸው የነበሩትን ልጃገረዶች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲነጋገሩ ግን መስማማት አልቻሉም ነበር። ማስታወሻው እንዲህ ይላል

"እርስ በርሳቸው መጣላት ጀመሩ። አንድ ትንሽ ልጅ ከመካከላቸው 'ማቃጠል አለብን' አላቸው። 'አይሆንም ወደ ሳምቢሳ መውሰድ አለብን' አለ ሁለተኛው። ሌላኛው ሰው ደግሞ 'አይ አይሆንም እንደሱ አናድርግ' አለና 'እንምራቸውና ከዚያ ወደ ቤተሰቦቻቸው ቤት እንሂድ' አለ። እየተከራከሩም ሳለ አንደኛው 'አይሆንም ባዶ መኪና ይዤ መጥቼ ባዶ መኪና ይዤ አልመለስም፣ ባይሆን ወደ [አቡባከር] ሼኮ [የቦኮ ሃራም መሪ] ይዘናቸው ከሄድን ምን ማድረግ እንዳለበን ያውቃሉ። "

አንዳንዶቹ ሴቶች በታጣቂዎቹ መኪኖች ላይ ተጭነው ብዙዎቹ ደግሞ ሽጉጥ ተደቅኖባቸው ብዙ ኪሎሜትሮችን ከተራመዱ በኃላ የጭነት መኪኖች መጥተው አፈሷቸው።

ማስታወሻ ደብተሮቹን ማን ጻፋቸው?

  • ዋና ጸሐፊዎቹ ፡ ናዖሚ አዳሙ እና ሣራ ሳሙኤል
  • ሮዳ ፒተር፣ ሳራቱ አዩባ እና ማርጋሬት ያማ አነስተኛ አስተዋጽዎችን አበርከተዋል
  • ከመካከላቸው አራቱ ከብዙ ድርድሮች በኃላ በግንቦት 2009 ተለቀዋል
  • ሣራ ሳሙኤል ባለፈው ዓመት ውስጥ አንዱን ታጣቂ ለማግባት ተስማምታ እስካሁን በእገታ ሥር ናት።

ወደ ቦኮ ሃራም መደበቂያ ደን እያመሩ ሳለ አንዳንድ ተማሪዎች ከጭነት መኪኖቹ እየዘለሉ መውረድ ጀመሩ። አንደኛዋ ታጋች ግን ለአጋቹ ነገረችው።

ድንገት ብቻዋን ትቀራለች ብላ ፈርታ ወይም ሥልጣንን ለማክበር ወይም ደግሞ በስቃይ ብቸኛ ላለመሆን ሊሆን ይችላል ትላለች ጸሃፊዋ።

"መኪናው ውስጥ የነበረችው አንደኛዋ ልጅ 'ሹፌር አንዳንድ ሴቶች ለማምለጥ እየዘለሉ ነው' አለችው። ሹፌሩም በሩን ከፈተና በእጅ መብራት ቢፈልጋቸውም ማንንም ማየት አልቻለም። ስለዚህ አንድ ቦታ ሳይንቀሳቀሱ መቀመጥ እንዳለባቸው ተናገሩ። ካሁን ወዲህ እሷም ሆነች ማንም ሲዘል ቢያዝ በሽጉጥ እንገልሻለን'አሉ''

በቦኮሃራም የታገቱት ልጃገረዶች ከብዙ ስቃይ በኋላ ሳምቢሳ ደን ደርሰዋል።

የክፋት ተንኮሎች

ታጣቂዎቹ የታገቱት ሴቶች ላይ የተለያዩ የክፋት ዘዴዎችን በመጠቀም ያስፈራሯቸው ነበር።

ምንም ውሸት ቢሆንም ወላጆቻቸው በቦኮ ሃራም ቁጥጥር ሥር እንደሆኑ ይነግሯቸው ነበር።

በአንድ ወቅት ክርስቲያኖቹን ከሙስሊም ሴቶች ለይተው ኃይማኖታቸውን ወደ እስልምና ካልቀየሩ በቤንዚን እንደሚያቃጥሏቸው ነገሯቸው።

"ወደኛ መጡና 'ሙስሊም ለሆናችሁ የጸሎት ሰዓት ደርሷል' አሉ። ከጸለዩ በኃላ 'ሙስሊም የሆናችሁ በአንድ በኩል ክርስቲያኖች ደግሞ በዚያኛው ማዶ ሁኑ'አሉን ፤ ከዚያ መኪናው ውስጥ ጄሪካን ስናይ ቤንዚን መሰለን፥ እነሱም 'ስንቶቻችሁ ወደ እስልምና ትቀየራላችሁ?' አሉን። ብዙዎቹ በፍራቻ ምክንያት ከመካከላችን ተነስተው ወደ ውስጥ ገቡ... እነሱም መልሰው 'የቀራችሁት በሙሉ መሞት ስላማራችሁ ነው ሙስሊም መሆን የማትፈልጉት? እናቃጥላችኋለን' አሉንና ቤንዚን የያዘ መስሎን የነበረውን ጄሪካን ሰጡን። ቤንዚን ግን አልነበረም ... ዉሃ ነበር።''

የሴቶቹ የ'መደፈር' ጉዳይ

ከዚህ በፊት የቺቦክ ትምህርት ቤት ታጋች ልጃገረዶች ቃላቸውን ሲሰጡ አልፎ አልፎ የጋብቻ ጥያቄዎች ቢቀርቡላቸውም ወሲባዊ ጥቃትም እንዳልደረሰባቸውና ያለፍላጎታቸው እንዲያገቡ እንዳልተደረጉ ተናግረዋል።

የምስሉ መግለጫ,

ልጃገረዶቹ ማስታዎሻዎቻቸውን በመቅበር ወይ በውስጥ ሱሪያቸው በመወሸቅ ይደብቋቸው ነብር

እነዚህ ማስታወሻዎችም ልጃገረዶቹ እንደተደፈሩ ተደርጎ በተለያዩ ሚዲያዎች መወራቱ ታጣቂዎቹን በእጅጉ አስቆጥቷቸው እንደነበረ ይጠቅሳሉ። የታጣቂዎቹ አለቃ የሆነው አቡበካር ሼኮ በተደጋጋሚ ንዴቱን ግልጽ አድርጓል። እሱም በመጀመሪያ በተቀዳ መልዕክት ለልጃገረዶቹ መልዕክት አስተላልፏል።

"ከዚያም በማታ አሰባሰቡንና የተቀዳ ካሴት አብርተው ይሰብኩልን ጀመር። ካሴቱ ከአለቃቸው ከአቡበከር ሼኮ መሆኑንም ገለጹልን... እሱም የፈጣሪን መንገድ ለማስተማር ብናግታችሁ ወላጆቻችሁ፣ ትምህርት ቤታችሁና መንግስታቸሁ እንደደፈርናቸና መጥፎ ነገር እንዳደርግናችሁ እየተናገሩ እያለቃቀሱ ነው። እኛ ግን የአላህን መንገድ ልናስተምራችሁ ነው ያመጣናችሁ። "

የፎቶው ባለመብት, AFP

የታጣቂዎችን ፍላጎት ላለማነሳሳት ሂጃብ መልበስ

ታጣቂዎቹ ምንጊዜም ቢሆን ሴቶቹ ፍላጎታቸውን እንዳይፈታተኑ ይጠይቋቸው ነበር ፤ እናም ሰውነታቸውን በሂጃብ እንዲሸፍኑ ይነግሯቸዋል።

'' ቁርዓን ከፍቶ ማንበብ ጀመረ፤ ከዚያም ከአንድ ቦታ ይህን አነበበልን 'ለጂሃድ ውጊያ የታያዘ ሰው ሁሉ የራሳችሁ ነው፤ በዛ ሰው ላይ የፈለጋችሁትን ነገር ሁሉ ማድረግ ትችላላችሁ'... ሆኖም እነሱ ሰውነታችንን በማየት በእኛ ላይ ኃጢዓት እንዳይሰሩ ወይም ሌላ ክፉ ነገር እንዳይፈጽሙ በማሰብ ሂጃብ ሰጡን''

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጋብቻ ጥያቄዎች

ማስታወሻዎቹ ከታጣቂዎቹ የሚቀርቡት የጋብቻ ጥያቄዎች የሚደጋገሙና የሚያስገድዱ እንደነበሩ ይገልጻሉ።

"አንደኛዋ ልጅ ዕቃ ፈልጋ ወደ ክፍል ስትገባ ማላም አህመድ የተሰኘው አንደኛው ታጣቂተከትሏት ገብቶ ለጋብቻ ቢጠይቃት እምቢ አለችው። መልሶ ግን "ስለ ጋብቻ የራስሽ ውሳኔ ምንድን ነው? አላት""እሷም በድጋሚ እምቢ አለችው። 'በቺቦክ እማርበት ከነበረ የሴቶች የመንግሥት ትምህርት ቤት ወደ ሳምቢሳ አመጣችኝ፤ አሁን ደግሞ ስለ ጋብቻ ትጠይቁኛላችሁ' አለች። እንዴት ልታገባ ትችላለች በዚያ ላይ እናቷ አባቷአክሰቶቿና ጓደኞቿ አያውቁም። ከዚያ 'አላገባም ብትልና ባለችበት አምላኳን ብቻዋን ብታመልክ ጥሩ አይደለም' ወይ ብላ ጠየቀችው። እሱም "መጥፎ ነው" ብሎ መለሰላት።"

አንዳንዶች ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ ግፊት ተደርጎባቸዋል።

"ሰዎቹ በሁለት ሃይሉክስ መኪኖች ሲመጡ አይተናቸዋል። እንደመጡም ከመካከላችን ማግባት የሚፈልጉ ካሉ ጠየቁ። ከዚያም እስልምናን የተቀበልነው በግድ ማግባት እዳለብን ነገሩን፤ በተለይ ይማኖቱን በሙሉ ልብ የተቀበልን ከሆነ። ምላሽም እንድንሰጣቸውም ግማሽ ሰዓት ጠበቁን። ከዚያ አንድ ሙሉ ሰዓት ጠበቁን ማንም መልስ አልሰጣቸውም። "

ጋዜጠኛዋ እንደምትለው ናዖሚ አዳሙ ለማግባት ፈቃደኛ ያልሆኑትን እንደ ባሪያ ነበር እንደሚመለከቷቸው ነግራታለች።

"በየቀኑ ይደበድቡን ነበር፤ እንድናገባቸው ይጠይቁንና እምቢ ካልን ይደበድቡን ነበር። ልብስ እናጥባለን፣ ዉሃ ከወንዝ እንቀዳለን፣ ለሚስቶቻቸው ደግሞ ሁሉን ነገር እናደርግ ነበር። ባሪያዎቻቸው ነበርን።"

የፎቶው ባለመብት, AFP

ሴት ልጆቻችንን መልሱ' [ብሪንግ ባክ አወር ገርልስ] የተሰኘው በዓለም ዙሪያ የተደረገው እንደ ሚሼል ኦባማና ሌሎችንም ታዋቂ ሰዎችን ያሳተፈ እንቅስቃሴ ቢደረግም በደኑ አካባቢ የነበሩ ነዋሪዎች ግን ልጃገረዶቹን በመመለስ ጣልቃ መግባት ካለመፈለጋቸውም በላይ ጠፍተው ያገኟቸውን መልሰው ለቦኮ ሃራም አስረክበዋል።

"አንዳንድ ሴቶች ሮጡ፤ ለማምለጥ ቢሞክሩም እንኳን ሊሳካላቸው አልቻሉም። አንዳንድ ሰዎችም አሰሯቸው።የተያዙበት መንገድ ደግሞ አምልጠው በአቅራቢያ ወደነበረ ሱቅ ውሃና ብስኩት ሲለምኑ ነው። 'ማን ናችሁ ከየት ነው የመጣችሁት? 'ብለው ሲጠይቋቸው በቦኮ ሃራም ከመንግሥት ሴቶች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ታግተው እንደነበር ነገሯቸው። ሰዎቹ ግን 'እነዚህ የሼኮ ልጆች አይደሉ እንዴ? ' ብለው ተጠያየቁ ፤ ከዚያም ምግብና የሚተኙበት ቦታ ሰጧቸውና በማግስቱ ለቦኮ ሃራም አስረከቧቸው። በምሽት ነበር ወደ ሳምቢሳ ያመጧቸው... እነሱም አንገታቸውን እንደሚቆርጡ አስፈራሯቸውና ገረፏቸው።"

የፎቶው ባለመብት, STRINGER

የወቀሳው ጫወታ

ከልጃገረዶቹ ማንም ሳይቀር ሁሉም እምነታቸውን ወደ እስልምና ለመቀየር ከተስማሙ ወደ ቤት ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መቀላቀል እንደሚችሉ ተነግሯቸው ነበር።

እናም በዚህ ኃሳብ የተስማሙት ልጃገረዶች እምቢታን መርጠው እገታውን ያስቀጠሉትን ልጃገረዶችን ተጠያቂ ያደርጉ ነበር።

"እስልምናን የማይቀበሉት 'እንደ በግ፣ላምና ፍየል የሚቆጠሩ ናቸው' በሚል እንደሚገድሏቸው ይዝቱ ነበር። ከዚያም ከታጣቂዎቹ አንዱ የሆነው ማላም አባ እስልምናን ያልተቀበሉት በአንድ በኩል እንዲቆሙ ተናገረ።ለመቀበል ከተስማሙት ጋር እንዳይቀላቀሉም አዘዘ። 'ለእነርሱ ሌላ ቦታ ይዘጋጅላቸዋል' ቢልም ሌላኛው ደግሞ የእርሱን ሃሳብ በመቃወም አንድ ላይ መቆየት እንዳለብን ተናገረ። ከአንድ ሳምንት በኋላ ኃይማኖታችንን ለመቀየር ያልተስማማነው 'ወደቤታችን ከመሄድ እየገደብን ያለነው እኛው ራሳችን ነን' አልን''

የፎቶው ባለመብት, AFP/BOKO HARAM

የምስሉ መግለጫ,

የልጃገረዶቹ ፊት ደብዘዝ ተደርጓል ምክንያቱም የተወሰኑት የቦኮ ሃራም ታጣቂዎችን በማግባታቸው ከተፈቱ በኃላ መገለል ደርሶባቸዋል

ቪድዮዎቹ እንዴት ተቀዱ?

የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች በየጊዜው ያገቷቸውን ልጃገረዶች በቪድዮ እየቀረጹ ይለቁ ነበር። ይህ ደግሞ ስለ ቀረጻው የውስጣዊ እይታ የሚሰጠን ክፍል ነው።

" ከአንድ ቀን በፊት መጥተው ከመካከላችን 10 የሚሆኑትን ከዛፉ ሥር በቪድዮ ቀረጿቸው። አንድ በአንድ እየነጠሉ ስማቸውንና ስለቤተሰቦቻቸው ጥያቄ መጠየቅ ጀመሩ። ከዚያም 'ጉዳት አድርሰንባችኋል? 'ብለው ሲጠይቁን እኛም 'አይ' ብለን መለስን። ለቤተሰቦቻችንና ለመንግሥት ምን እያደረጉን እንደሆነ እንድንናገር ጠየቁን። ምክንያቱም መንግሥትና ቤተሰቦቻችን እየደፈሩንና እየረበሹን እንደሆነ ስለተናገሩ። ''

"ከኛ መካከል አንደኛዋን ወስዶ 'ካገትንሽ ሰዓት አንስቶና እዚህ ቦታ ካመጣንሽ ጀምሮ ደፍረንሽም ሆነ አብረንሽ ተኝተን እናውቃለን?' ብሎ ሲጠይቃት እሷም 'አይ' ብላ መልስ ብትሰጠውም በድጋሚ ጠየቃት 'ለቤተሰቦችሽና ለመንግሥት ምን እያደረግንልሽ እንደሆነና እንዴት እየተንከባከብንሽ እንደሆነ አሳያቸው። ''

ታጣቂዎቹ ዜና በጥሞና ይከታተሉ ነበር

ብዙውን ጊዜ ቪድዮዎቹን ዜና ከተከታተሉ በኃላ ነበር የሚቀርጹት።

"ትንሽ ቆይተው ቢቢሲ ሃውዛን [በናይጄሪያ ቋንቋ] ያዳምጡ ጀመር። ልክ ሬድዮ አዳምጠው እንደጨረሱ አንድ በአንድ ጠሩን። አንዳንዶቻችንን እንድንንበረከክ የተቀረነው ደግሞ እንድንቀመጥ አደረጉና የምናነበውን ሰጥተው መቅረጽ ጀመሩ። ከዚያ ከቁርዓን አነበብን።''

ማስታወሻ ደብተሮቹን የጻፏቸው ልጃገረዶች የት ደረሱ?

ናኦሚ አዳሙና ሌሎች ሶስት ጸሃፊዎች ሮዳ ፒተር፣ ሳራቱ አዩባና ማርጋሬት ያማ ባለፈው ሚያዚያ ተፈትተዋል።

መስከረም ላይ በናይጄሪያ በሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ እንዲማሩ ተልከዋል።

አዳሙ ለቤተሰቦቿ ከሰባቱ አንዷ ስትሆን ማስታወሻዎቹን የጻፈችው ቤተሰቦቿን በማሰብ እንደሆነ ለጋዜጠኛ አዳዎቢ አጫውታታለች።

"ማስታወሻውን የጻፍኩት ወንድሞቼ፣ እህቶቼና ወላጆቼ እንዲያዩት ብዬ ነው" ትላለች

የምስሉ መግለጫ,

የናኦሚ እናት የማስታወሻ ደብተሩን ይዘው

የናኦሚ እናት ኮሎ ይባላሉ እሳቸው ማንበብ ባይችሉም ስለማስታወሻ ደብተሮቹ ይበልጥ ማወቅ እፈልጋለሁ ይላሉ።

ብዙውን የማስታወሻ መልዕክቶች ሳራ ሳሙኤል ብትጽፋቸውም ገና ስላልተመለሰች ጓደኛዋ ናኦሚ አዝናለች።

"እንደተጎዳሁ ይሰማኛል። እስካሁን እሷን ነው የማስበው። ''

ሳራ በታገቱ በሁለተኛው ዓመት ነበር የናይጄሪያ ወታደራዊ ኃይል ሲከባቸውና የቦኮ ሃራም መተዳደሪያ አቅርቦት ሲዘጋባቸው በፍርሃት ለማግባት የተስማማችው።

በማግባቷም ምክንያት የነበሩበትን ካምፕ ከባለቤቷ ጋር ምግብ ወደሚገኝበት አካባቢና የተሻለ ሕይወት ወደሚመሩበት ጥላ ለመሄድ ተገደደች።

ከመካከላቸው ትዳር ከመሰረቱት ውስጥ እስካሁን አንዳቸውም አልተለቀቁም።

የሳራ አባት አቶ ሳሙኤል ያጋ ለጋዜጠኛዋ የመጀመሪያ ልጁ መጽሃፏ ብዙም እንዳላስደነቀው አጫውቷታል።

"ሁሌ እንዳነበበች ነበር። አንዳንዴ መጽሐፍ እንደያዘች እንቅልፍ ይዟት ይሄድ ነበር'' በለዋል ።

በማስታወሻ ድብተሯ የመጨረሻው ገጽ ላይ የአምስት ወንድምና እህቶቿን ስሞች ጠቅሳለች በመጨረሻም " የአባቴ ስም ሳሙኤል ሲሆን እናቴ ደግሞ ርብቃ ትባላለች '' ብላ ጽፋለች።

መርሳት የማትፈልግ ይመስል ነበር።