ስለምን የሰው ሕይወት የቀጠፈው የላስ ቬጋስ ጥቃት 'ሽብርተኝነት' አልተባለም?

stephen padock

የፎቶው ባለመብት, CBS NEWS

59 ሰዎች በአንድ ታጣቂ የተገደሉበት ጥቃት በአሜሪካ ዘመናዊ ታሪክ አስከፊ ክስተት እነደሆነ ቢነገርም፤ የሽብር ጥቃት ነው አልተባለም። ለምን?

እሁድ ዕለት የሙዚቃ ድግስ በታደሙ ሰዎች ላይ በ64 ዓመቱ ስቴፈን ፓዶክ ተፈፅሞ የ59 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውና ከ500 በላይ ሰዎችን ያቆሰለውን ጥቃት የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ድርጊቱን የሽብር ጥቃት ብለው እንደማይጠሩት ለማሳወቅ ጊዜ አላጠፉም ነበር።

ነገር ግን ብዙ ሰዎች፤ ይህ በአሜሪካ ታሪክ የከፋ ሆኖ በርካታ ሰዎችን የገደለ ጥቃት ከሽብር ድርጊት ውጪ ምን ተብሎ ሊጠራ ይችላል? በማለት ይጠይቃሉ።

ፓዶክን ሽብርተኛ ብሎ ከመጥራት ይልቅ እንዲሁ እንደቀላል 'ብቸኛው ጥቃት ፈፃሚ' ፣ 'ተኳሹ' ወይም 'ታጣቂው' ተብሎ መጠራቱን በመቃወም በርካቶች በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ ትችትን እንዲሰነዝሩ አድርጓቸዋል።

ሌሎች እንዲያውም 'ሽብርተኛ' የሚለው ስያሜ ለሙስሊሞችና ነጭ ላልሆኑ ሰዎች ብቻ ጥቅም ላይ እየዋለ፤ ዘርንና ፖለቲካን መሰረት እንዲያደርግ ሆኗል እስከማለት ደርሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ስለዚህ ሽብርተኝነት ትርጉሙ ምንድን ነው?

አብዛኞቹ የሽብርተኝነት ትርጓሜዎች የሚያተኩሩት ድርጊቱ ባስከተለው ውጤት ላይ ሳይሆን ድርጊቱ እንዲፈፀም ያነሳሳው ምክንያት ላይ ነው። የአሜሪካ ፌደራል ህግ ስለሽብር ባስቀመጠው ብያኔ 'ፖለቲካዊ ወይም ማህበራዊ ዓላማዎችን ለማሳካት ሲባል በሰዎች ወይም በንብረት ላይ ህገ-ወጥ ኃይልና ድርጊትን በመጠቀም ማስፈራራትና መንግሥትን ማስገደድ' ይለዋል።

ስለዚህም ምንም እንኳን ይህ ጥቃት በአሜሪካ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ እጅግ አደገኛው ቢሆንም፤ የጥቃቱ ፈፃሚ አላማ ነው ትኩረት የተሰጠው።

ሰኞ ዕለት የላስ ቬጋስ ፖሊስ ኃላፊ እንደተናገሩት "በዚህ ጊዜ የጥቃቱ ፈፃሚ የሚከተለው እምነት ምን እንደሆነ አናውቅም" ብለዋል። የኤፍቢአይ ልዩ ወኪል የሆኑት አሮን ሩስ በበኩላቸው እንዳሉት መሥሪያ ቤታቸው በጥቃቱ ፈፃሚና በዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖች መካከል ግንኙነት እንዳለ የሚያሳይ ነገር አላገኘም።

በዚህ መሰረትም ፓዶክ ሽብርተኛ ተብሎ አይጠራም ማለት ነው።

ነገር ግን የላስ ቬጋስ ከተማ ግዛት ውስጥ የምትገኘው ኔቫዳ ሽብርተኝነትን በተመለከተ የተለየ ትርጓሜ አላት። 'ሽብርተኝነት በህዝብ ላይ ከፍ ያለ አካላዊ ጉዳት ወይም ሞትን ለማድረስ ታስቦ ማስገደድና ኃይልን መጠቀም ወይም ለመጠቀም የመሞከር ማንኛውም ድርጊት ነው'' ይላል።

ይህም ደግሞ አሁን ከተፈፀመው ጥቃት አንፃር በማያሻማ መልኩ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል።

አንዳንድ ሪፐብሊካንና ዴሞክራት ፖለቲከኞች ግን ድርጊቱን የሽብር ተግባር ነው ብለው ለመጥራት አላንገራገሩም። በእርግጥም በዚም አለ በዚያ ዋናው ነገር ድርጊቱ በስሙ መጠራቱ ነው።