ሳዑዲ አረቢያ የጣለችው እገዳ ለየመን ጥፋት ነው

የመን ግጭት Image copyright ABDO HYDER

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የዓለምአቀፉ ቀይ መስቀል ማሕበር በየመን ያለውን ሁኔታ ለሚሊዮኖች ሕይወት አደጋ ነው ሲሉ ገልፀውታል።

ሳዑዲ አረቢያ የየመን ሁቲ ታጣቂዎች በኢራን እየታገዙ ነው ስትል ትወቅሳለች፤ ቴህራን ከዚህ ተግባሯም እንድትቆጠብም አሳስበዋል።

ኢራን በበኩሏ ለሁቲ ታጣቂዎች ምንም ዓይነት እርዳታ እያደርኩ አይደለም ስትል ክሱን ውድቅ ታደርጋለች።

ዕለተ ቅዳሜ ወደ ሳዑዲ ዋና ከተማ ሪያድ የተተኮሰ ሚሳዔል በሳዑዲ ተመቶ እንደወደቀ ይታወሳል።

የሳዑዲ ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን "ለአማፂያን የጦር መሣሪያ ማቅረብ ከጦርነት አይተናነስም" ሲሉ ተሰምተዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ አማባሳደር ኒኪ ሄሊ ሚሳዔሎቹ የኢራን ሳይሆኑ አይቀሩም ብለዋል። ኢራን የመንግሥታቱ ድርጅትን ሕግ እየጣሰች ነው፤ ተጠያቂ ልትሆንና እገዳ ሊጣልባትም ይገባል ሲሉ ተድምጠዋል።

ኢራን ወቀሳውን "የሚሳዔል ጥቃቱ አማፅያኑ በሳዑዲ እየደረሳበቸው ያለውን ወረራ ለመዋጋት ያደረጉት የተናጥል ትግል እንጂ የቴህራን እጅ የለበትም" ስትል አጣጥላዋለች።

Image copyright AP

በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ኃይል የሚሳዔል ጥቃቱን ተከትሎ ወደ የመን የሚያስገቡ በሮችን በጠቅላላ ላልተወሰነ ጊዜ ዘግቷል። ነገር ግን ሰብዓዊ እርዳታ በጥብቅ ፍተሻ አልፎ ሊሰጥ እንደሚችል አስታውቋል።

ነገር ግን ጄኔቫ የሚገኘው የቢቢሲው ኢሞገን ፎክስ እርዳታ ድርጅቶች የድንበሮቹ መዘጋትን ተከትሎ ቁጣቸውን እየገለፁ እንደሆነ ዘግቧል።

የዓለምአቀፉ ቀይ መስቀል ማሕበር 900 ሺህ ሰዎችን ያጠቃውን ኮሌራ ለመመከት ወደ የመን ያስጫነው የክሎሪን ክኒን ደንበር መሻገር እንዳልቻለ ተናግሯል።

"እኚህ መግቢያ በሮች እስካልተከፈቱ ድረስ በየመን ያለው ቀውስ ሊፈታ አይችልም። ሃገሪቱ ከአሁን በፊት ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ ትልቅ ችግር ውስጥ ነች" ሲሉ የቀይ መስቀሉ ጄንስ ላርክ ይናገራሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰባት ሚሊዮን የመናውያን የረሃብ አደጋ ላይ ናቸው ሲል ማስታወቁ አይዘነጋም።

ሃገሪቱ ከውጭ በሚገባ ምግብ ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ ስትሆን አሁን ላይ ግን ነዳጅም ሆነ መድሐኒት ለማስገባት እጅግ አዳጋች ነው።

በየመን ግጭት እስካሁን ደረስ 8 ሺህ 670 ሰዎች የሞቱ ሲሆን 49 ሺህ 960 ሰዎች በአየር ድብደባ ቆስለዋል፤ እንደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለፃ።