ካለሁበት 9፡ በኑሮዬ ደስተኛ ብሆንም ለቁርስ ቋንጣ ፍርፍር ባገኝ እወዳለሁ

ሳሙኤል አርዓያ Image copyright SAMUEL ARAYA

ሳሙኤል አርዓያ እባላለሁ። በደቡብ ምስራቅ እስያ በምትገኘው ሲንጋፖር ነው የምኖረው።

ከኢትዮጵያ ከወጣሁ ብዙ ዓመታት አስቆጥሬያለሁ። ወደዚህ ሀገር ከመምጣቴ በፊት ፈረንሳይ ለአሥር ዓመታት ያህል በትምህርት እና በሥራ አሳልፌያለሁ።

ወደ ሲንጋፖር የመጣሁት ሳይፔም ተብሎ በሚጠራ ኩባንያ ባገኝሁት የሥራ ዕድል ነው። በዚህ ድርጅት ኤፍ ፒ ኤስ ኦ ካዎምቦ "FPSO KAOMBO'' ለተባለው ፕሮጄክት የጥገና መሃንዲስ ሆኜ ነው የምሥራው።

ከባህር ነዳጅ አውጥቶ ለማመላለስ በተዘጋጁ መርከቦች ላይ ያሉትን መሣሪያዎች በመቀየር እና የሚያስፈልጓቸውን ተጨማሪ መሣሪያዎች በመጨመር የመቆጣጠሩን ሥራ አከናውናለሁ።

ሲንጋፖር በጣም ውድ ከተማ ሆና አግኝቻታለሁ። ከመጣሁ አንስቶ በጣም የሚያስገርመኝ ያለው ሥርዓት፣ የሰዉ ሕግ አክባሪነትና ሲንጋፖር በጣም ንፁሕ ሀገር መሆኗ ነው። ሁሉም ነገር ሥርዓቱን የጠበቀና ለሁሉም ሰው ተደራሽ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጁ የተሟሉ የሕዝብ መገልገያዎች መኖራቸውም እንድደመም አድርጎኛል።

Image copyright SAMUEL ARAYA
አጭር የምስል መግለጫ ዲም ሱም የተባለው ምግብ በእንፋሎት የሚበስል ሳምቡሳ የሚመስል ነው።

እስካሁን የኢትዮጵያ ምግብ ፈልጌ ማግኘት አልቻልኩም። አምሮቴን ለመወጣት ልመገብ ብል እንኳን ቅርብ የሚባለው የኢትዮጵያ ምግብ ቤት ወደ 2000 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ታይላንድ ርዕሰ መዲና ባንኮክ ነው የሚገኘው። ስለዚህ "ዲም ሱም" እበላለሁ። ዲም ሱም የተባለው ምግብ በእንፋሎት የሚበስል ሲሆን ሀገር ቤት የሚሸጠውን ሳምቡሳ ይመስላል፤ ተመራጭ ምግቤም ሆኗል።

ለአሥር ዓመታት ከኢትዮጵያ ውጪ ስለኖርኩኝ ከሀገር ቤት ምን እንደሚናፍቀኝ ለማወቅ ራሴን እጠይቃለሁ። ምላሽ ለማግኘት ግን ይከብደኛል ምክንያቱም የሚናፍቀኝን ብናገር ቤተሰብህን ረሳህ ተብዬ ልወቀስ ነው።

ሆኖም ግን ሁሌም ስለኢትዮጵያ ሳስብ ዓመት በዓል ነው በሃሳቤ የሚመጣው። ጠዋት ተነስቶ ቤተ-ክርስትያን ደርሶ፣ ጎረቤት ሄዶ ቁርስ መብላቱ፤ ችቦ ማብራቱ ... ደግሞም ሽታው፤ ጫጫታው... በአጠቃላይ ወከባው ይናፍቀኛል።

ኢትዮጵያ ለጉብኝት እንኳን ከተመለስኩኝ ቆየት ብያለሁ። ቢሆንም የማስታውሳቸውና በአዕምሮዬ የሚመላለሱ ብዙ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ብሔራዊ ትያትር ጋር ያለው አንበሳ፣ ቸርችል ጎዳናና ለገሃር አካባቢ ያለው ሁሉ ትዝ ይለኛል።

እንደዚያም ሆኖ ግን የቅርብ ትውስታዬ የፈረንሳይ ሀገር ቆይታዬ ነው። በፈረንሳይና በሲንጋፖር መካከል ብዙ ልዩነቶች አላየሁም።

Image copyright SAMUEL ARAYA
አጭር የምስል መግለጫ በሳሎኔ በረንዳ በኩል በመስኮቴ ስመለከት ደስ የሚል ስሜት ይፈጥርብኛል

ያም ሆኖ እንደ ሲንጋፖር ከተማ በሕንፃ የተሞላች ከተማ ያለች አይመስለኝም። እኔ የምኖርበት ሕንፃ ዙርያውን በሌሎች ሕንፃ የተከበበ ቢሆንም ደስ ሚል ስሜት አለው። በሳሎኔ በረንዳ በኩል ስመለከት ደስ የሚል ስሜት ይፈጥርብኛል።

ሲንጋፖር የምታስጨንቅም ሆነ የምትጨቁን ከተማ አይደለችም። ሥርዓቱ እስከተጠበቀ ድረስ በጣም ግልጽና ነፃነትን የምታበረታታ ከተማ ሆና ነው ያገኘኋት። በተለያዩ ምክንያቶች የመጡ ብዙ የውጪ ዜጎችን የምታስተናግድ መሆኗም ሊሆን ይችላል እንደዚህ እንድትሆን ያደረጋት።

ያለማቋረጥ የሚያስደንቀኝ ግን ሥርዓቱ ነው። በሲንጋፖር መሬት ላይ ምንም አይነት ቆሻሻ መጣል አይቻልም።

በሕዝብ ማመላለሻ ላይ ምግብም ሆነ መጠጥ መጠቀም ክልክል ነው። በይበልጥ ደግሞ የሚያስደንቀው ማስቲካ በመንገድ ላይ ማኘክ መከልከሉ ነው። እጅግ በጣም ንፁህ ሀገር መሆኗ ሁሌም ያስገርመኛል።

የሲንጋፖር ነዋሪዎች በጣም ሕግ አክባሪ፣ ደግና ጨዋዎች ናቸው። በዚያ ላይ ሁሉም ስለራሱ እንጂ ስለሌላ ሰው ሕይወት ብዙ ትኩረት ሲሰጡ አላየሁም።

Image copyright SAMUEL ARAYA
አጭር የምስል መግለጫ ሳሙኤል በበረንዳው ላይ 'ሰልፊ' ተነስቶ

በኑሮዬ ደስተኛ ብሆንም ለቁርስ ቋንጣ ፍርፍር እንደጎደለብኝ ይሰማኛል።

ለማንኛውም ሰው ከተወለደበት ሀገር ወደ ሌላ ቦታ ሲጓዝ ብዙ ነገሮች ሊከብዱት ይችላሉ።

እኔ ግን ዕድለኛ ነኝ ምክንያቱም ፈረንሳይም ሆነ ሲንጋፖር ብቻዬን ሆኜ አላውቅም። ምንም ቢሆን ግን የማይታወቅ ሀገር ሲኬድ ፍራቻና ስጋት ይኖራል። የዛሬ አሥር ዓመት ከኢትዮጵያ ስወጣ ልጅነትም ስለነበር ብዙም አልተጨነኩም ነበር።

አሁን ደግሞ ተማሪም ስላልሆንኩ ውሳኔዎቼ በሙሉ ሊያስከትሉ የሚችሏቸውን ነገሮች በማስብ ትንሽም ቢሆን ጭንቀት ያድርብኛል።

በአጋጣሚ ሆኖ ሲንጋፖር ለመጀመሪያ ጊዜ ስመጣ የማውቀው ሰው ስለነበር ምንም አልተቸገርኩም ነበር። የሥራ ባልደረቦቼም አብረውኝ ስለነበሩ ያን ያህል አዲስ ሀገር እንደሚሄድ ሰው አላስፈራኝም ነበር።

ሲንጋፖር አድገዋል ከሚባሉት ሀገሮች መካከል አንዷ ስለሆነች ለአዲስም ሰው ቢሆን ሁሉም ነገር የተመቻቸ ስለሆነ ጫካ እንደመግባት አይደለም። ይህን ስል ደግሞ በትምህርቴም ሆነ በሥራዬ ጥሩ ደረጃና ደህና ኑሮ የምኖር ሰው ነኝ ብዬ ስለማስብ ተቸግሬያለሁ ለማለት አልችልም። ምክንያቱም ሀገር በሚቀየርበት ጊዜ አመጣጥ ይወስነዋል። ገንዘብ ካለ ሲንጋፖር ውስጥ ብዙ ዕድሎች ክፍት ናቸው።

Image copyright SAMUEL ARAYA
አጭር የምስል መግለጫ ሳሙኤል በኤርታ አሌ

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ብሆን ብዬ ሳስብ ኤርታ አሌ ከጓደኞቼ ጋር የፈረንጆችን አዲስ ዓመት ያከበርነው ይታወሰኛል። አሁን ደግሞ እራሴን እዚያ ባገኘው ደስታውን አልችለውም። እንደ ኤርታ አሌ ያለ ቦታ አይቼ አላውቅም። መቼም ደግሞ እንደዚህ አይነት ቦታ የማይ አይመስለኝም።

ለክሪስቲን ዮሐንስ እንደነገራት

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦

ካለሁበት 10፡ የምመኘው በአንድነታችን ተዋደንና ተከባብረን በኢትዮጵያዊነታችን እንድንኖር ነው

ካለሁበት 11፡ በእንግሊዝ ሃገር ትልቁ ችግር ብቸኝነት ነው

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ