በመቱ ዩኒቨርስቲ ብሔር ተኮር ውጥረት ነግሷል

ተማሪዎች

የትግራይ ክልል ተማሪዎች የሚደርስባቸውን ዛቻ እና ማስፈራሪያ በመሸሽ ከዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ መውጣታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የመቱ ዩኒቨርስቲ ኃላፊዎች በበኩላቸው ተማሪዎቹ ከግቢ መውጣታቸውን አረጋግጠው ''ትምህርትን ጥሎ ለመሸሽ የሚያበቃ በቂ ምክንያት ግን የለም'' ብለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የትግራይ ክልል ተማሪዎች ''በእኛ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ፍተሻ በሌሎች ተማሪዎች ይካሄድብናል'' ሲሉ ተናግረዋል።

ይህም ስጋት ያሳደረባቸው ተማሪዎች ከዩኒቨርስቲው በ150 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደምትገኘው የጋምቤላ ከተማ አቅንተው ለአንድ ሳምንት ያህል በዚያው ቆይተዋል።

ተማሪዎቹ እንደሚሉት የዩኒቨርስቲው ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች እና የጋምቤላ ክልል አስተዳደር ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት ተደርጎ ረቡዕ ዕለት ወደትምህርት ገበታቸው ለመመለስ ወስነው በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ቢደርሱም የመጡበት አውቶብሶች በድንጋይ ጥቃት ስለደረሰባቸው ተመልሰው ወጥተዋል።

''ችግሩን ለመቅረፍ ከዩኒቨርስቲው ጋር እየሰራን ነው'' የሚሉት የመቱ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ መክብብ ተማሪዎቹ ከጋምቤላ ሲመለሱ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ደረሰብን ያሉትን ጥቃት እውነትነትም አረጋግጠዋል።

የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አቶ አዲሱ አረጋ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ድርጊቱን '' የአብዛኛውን ተማሪ አቋም አይወክልም፤ በኦሮሞ ባህል እና ወግ ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው'' በማለት የኮነኑት ሲሆን ተማሪዎቹ ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡም አስጠንቅቀዋል።

የጥርጣሬ እርሾ

በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባቦራ ዞን ውስጥ የምትገኘው መቱ ከተማ የተለያዩ ብሔሮች ተስማምተው የሚኖሩባት መሆኗን ከንቲባዋ አቶ ኃይሉ አፅንዖት ሰጥተው ይናገራሉ።

አቶ ኃይሉ'' በከተማዋ የብሔር መልክ ያላቸው ግጭቶችም ሆነ ቅራኔዎች አልነበሩም'' ይላሉ።

ይሁን እንጂ ''ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች ላይ በተነሱ ጥቆማዎች መሰረት የግለሰቦች ቤት ላይ ፍተሻ ተካሂዷል'' ሲሉ ያስረዳሉ።

በከተማው የተካሄዱት ፍተሻዎች በኦሮሞ እና በትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች መካከል ጥርጣሬ እና ስጋትን ሳይፈጥሩ አልቀረም የሚሉት አቶ ኃይሉ፤ የኦሮሞ ተማሪዎች በግቢው ውስጥ ስጋት አለብን በማለት የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎችን ማደሪያ ክፍሎች ሲፈትሹ እንደነበረ ይገልጻሉ።

ጋምቤላ ደርሶ መልስ

የዩኒቨርስቲውን ግቢ ለቅው ከወጡት ተማሪዎች መካከል ከትግራይ ክልል የመጣው አብረሃ ዘውዱ (ለደህነነቱ ሲባል ስሙ የተቀየረ) ይገኝበታል።

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ከመቱ ወጥቶ ወደጋምቤላ ከተማ ያቀናው አብረሃ ''ሰልፎች በተካሄዱ ቁጥር የትግራይ ተወላጆች ከዩኒቨርስቲው ይውጡ የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ ይነሳል'' ሲል ያስረዳል።

"ወደማደሪያ ክፍሎቻችን እየመጡ 'እናንተ ተጠርጣሪዎች ናችሁ፤ ቦምብ ይዛችኋል፣ እንድንፈትሻችሁ ተፈቅዶልናል' ይሉናል'' ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

አብረሃ ''በግቢው ውስጥ የቀረ የትግራይ ተወላጅ ተማሪ የለም'' ይላል።

የዩኒቨርስቲው የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኦልቀባ አሰፋ ግን በዚህ አይስማሙም።

አቶ ኦልቀባ ከግቢው የወጡ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች ከመቶ እንደማይበልጡ በመግለጽ ግቢውን ጥለው ለመውጣት የሚያደርስ "በቂ ምክንያት አልነበረም፤ ለስጋት የሚዳርግ ምንም እንቅስቃሴ አልነበረም፤ አሁንም የለም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አብረሃ እንደሚለው ከሆነ አስራ አምስት ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲው አንመለስም በማለት ወደ አዲስ አበባ አቅንተዋል።

የዩኒቨርስቲው ኃላፊዎች እና የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን ለመፍታት እየተወያዩ ቢሆንም አብረሃ ግን "እኛ ከሁሉም በላይ ሕይወታችንን ነው የምንፈልገው፤ ለእኛ ትምህርት ሁለተኛ ነገር ነው፤ መመለስ ነው የምንፈልገው'' ሲል ይናገራል።

የዩኒቨርስቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኦልቀባ "ከመጀመሪያውም አንስቶ ግቢውን ጥለው እንዳይሄዱ ጥረት ስናደርግ ነበር፤ አሁንም ወደ ዩኒቨርስቲው ተመልሰው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማድረግ ከመምህራንም ከተማሪዎች ጋር ምክክር እያደረግን ነው" ይላሉ።

በትናንትናው ዕለት ሰልፍ የወጡ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው አመራሮች ላይ የተቃውሞ ድምጽ ያሰሙ ሲሆን፤ ከሰልፈኞቹ መካከል ተማሪው ቶሎሳ ጋሪ (ስሙ የተቀየረ) ይገኝበታል።

ቶሎሳ ሁሉም ተማሪ ወደ ዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ከመግባቱ በፊት ይፈተሻል፤ ''የትግራይ ክልል ተማሪዎች ግን አይፈተሹም ይህም ጥርጣሬ አሳድሮብናል'' ሲል ይናገራል።

"የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ለተቋሙ መርህ ታማኝ መሆን ባለመቻላቸው፥ በአመራራቸው ላይ እምነት እንዳይኖረን አድርጓል" ይላል ቶሎሳ፤ "በመሆኑም ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ጥያቄ አቅርበናል'' ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።

የዩኒቨርስቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኦልቀባ ተቃዋሚ ተማሪዎቹ የበላይ አካል መጥቶ እስኪያነጋግረን ድረስ ትምህርት አንጀምርም ባሉት መሰረት መማር ማስተማሩ ከትናንት ጀምሮ መቋረጡን ተናግረዋል።

Image copyright FACEBOOK/ADDISU AREGA

የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አቶ አዲሱ አረጋ አርብ ማምሻውን በፌስቡክ ገጻቸው ከተማሪዎቹ ጋር ባደረጉት ውይይት የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰኞ ህዳር አራት እንዲቀጥል፣ ማንኛውም ተማሪ የሚኖረውን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርብ እና የሚመለከተው አካል ለጥያቄው ምላሽ እንደሚሰጥ በመስማማት ተጠናቋል ብለዋል።

አቶ አዲሱ ተማሪዎቹ ወደ ግቢው ለመመለስ ስለመስማማታቸው ያሉት ነገር የለም።

ተያያዥ ርዕሶች