ስለ ሙጋቤ እና ዚምባብዌ ምን እየተባለ ነው?

ሙጋቤ እና ግሬስ ሙጋቤ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ሮበርት ሙጋቤ እና ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ

የአፍሪካ ሕብረት ''ለመንግሥት ግልበጣው እውቅና አይሰጥም።'' ሕግ-መንግሥታዊ ላልሆኑ የመንግሥት ለውጦችን የአፍሪካ ህብረትም ሆነ የደቡብ አፍሪካ የልማት ማሕበረሰብ እውቅና አይሰጥም ሲሉ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

የቀድሞ የዚምባብዌ የተቃዋሚ ፓርቲ አማካሪና ጠበቃ የሆኑት አሌክስ ማጋኢሳ ደግሞ ''ሙጋቤ እራሳቸው በፈጠሩት አውሬ ተበሉ'' ሲሉ ተናግረዋል።

• ''ሮበርት ሙጋቤ በቁጥጥር ስር ውለዋል፤ ደህንነታቸውም ይጠበቃል''

የአውሮፓ ሕብረት በዚምባብዌ ለተፈጠረው ቀውስ ''ሰላማዊ መፍትሄ ይሰጥ'' ሲል አሳስቧል። ''የጦሩ ጣልቃ ገብነት አሳስቦናል የሚመለከታቸው አካላት ሰላማዊ መፍትሄ ለማፈላለግ አብረው መስራት ይኖርባቸውል'' ይላል ሕብረቱ ያወጣው መግለጫ።

የደቡብ አፍሪካ መሪ ጃኮብ ዙማ እና የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሃመዱ ቡሃሪ ''ሰላም፣ መረጋጋት እና መከባበር'' በዚምባብዌ እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል። ፕሬዝዳንት ቡሃሪ በሃገሪቱ አላስፈላጊ ደም መፋሰስ እንዳይከሰት ሁሉም የበኩሉን ይወጣ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ቻይና በበኩሏ ''ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው'' ብላለች። የዚምባብዌ ትልቋ የንግድ አጋር የሆነችው ቻይና ምዕራባውያን ሃገራት በዚምባብዌ ላይ ማዕቀብ ሲጥሉ ቻይና ግን የንግድ አጋርነቷን አጠናክራ ቆይታለች። የቻይና የውጪ ጉዳይ ቃል አቀባይ ''የቻይና አጋር በሆነችው ዚምባብዌ እየተፈጠረ ያለውን በቅርበት እየተከታተልን ነው። የሚመለከታቸው አካላት የሃገሪቱን የውስጥ ጉዳዮች አግባብነት ባለው መልክ ይመለከቱታል ብለን እናምናለን'' ብለዋል።

የእንግሊዝ እና የአሜሪካ መንግሥታት ዜጎቻቸው አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክረዋል።

• ጦሩ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያን ከተቆጣጠረ በኋላ ''መፈንቅለ መንግሥት አይደለም'' ብሏል

በሃራሬ የሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ "ሁኔታዎች እስኪረጋጉ ድረስ በቤቶቻቹሁ ቆዩ" በማለት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ የእንግሊዝ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ቦሪስ ጆንሰን ''ሁላችንም የበለጸገች እና ስኬታማ ዚምባብዌን ማየት ነው የምንሻው። ዋናው ነገር ሁሉም እራሱን ከግጭት መቆጠቡ ነው'' ብለዋል።

በሃራሬ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ደግሞ ባለው አለመረጋጋት ምክንያት ረቡዕ ዕለት ዝግ ሆኖ እንደሚቆይ አስታውቆ ሌላ መግለጫ እስኪወጣ ድረስ በዚምባብዌ የሚገኙ አሜሪካዊያን ባሉበት እንዲቆዩ መልዕክት አስተላልፏል።

Image copyright Trendsmap

እንደ ትሬንድስማፕ (Trendsmap) ዘገባ ከሆነ የማሕበራዊ ሚዲያ በሆነው ትዊተር ላይ ዚምባብዌን የሚመለከቱ በርካታ ዜናዎች እና ውይይቶች በስፋት እየተሰራጩ ነው። በምስሉ ላይ መመልከት እንደሚቻለው #Mugabe እና #Zimbabwe በመጠቀም በርካቶች በጉዳዩ ላይ እየተወያዩ ይገኛሉ።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ