በዚምባብዌ 'መፈንቅለ መንግሥት' የተካሄደ ይመስላል ሲል የአፍሪካ ህብረት ገለጸ

Soldier direct traffic in Harare Image copyright Reuters

የዚምባብዌ ጦር ስልጣን የተረከበበትና ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤን በቁጥጥር ስራ ያዋለበት መንገድ " መፈንቅለ መንግሥት ይመስላል" ሲል የአፍሪካ ህብረት አስታውቋል።

የህብረቱ ኃላፊ አልፋ ኮንዴ እንዳሉት የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩ በአስቸኳይ ህገ-መንግሥታዊ መፍትሔ እንዲሰጠው ያስፈልጋል ብለዋል።

ጦሩ በበኩሉ መፈንቅለ መንግሥስት እንዳልተካሄደ በመግለጽ ሙጋቤ ደህንነታቸው እንደተጠበቀ እና ትኩረት የተደረገው በዙሪያቸው በሚገኙ ወንጀለኞች ላይ መሆኑን አስታውቋል።

ጦሩ ጣልቃ የገባውም ሙጋቤን ማን ይተካቸዋል በሚለው የስልጣን ፍትግያ መሃል ነው።

ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ባለፈው ሳምንት ከኃፊነት የተነሱ ሲሆን ይህም ቀዳማዊ እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ተተኪ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ ነበር።

ይህ ውሳኔ ግን የጦሩ ከፍተኛ ኃላፊዎች የመገፋት ስሜት እንዲኖራቸው አድርጓል።

ፕሬዝዳንት ሙጋቤ ሃገራቸው እ.አ.አ በ1980 ነጻነቷን ከእንግሊዝ ከተቀዳጀች ጀምሮ በፖለቲካው ውስጥ ትልቅ ሚና ነበራቸው።

የጊኒ ፕሬዝዳንት የሆኑት ኮንዴ "ጦሩ የሃገሪቱን ስልጣን ለመያዝ ሙከራ አድርጓል" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩ "በጣም አሳሳቢ" እንደሆነበት ገልጸው፤ "ለሃገሪቱ ህጋዊ ተቋማት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ" ተናግረዋል።

የቢቢሲዋ አን ሶይ እንደምትለው እ.አ.አ በ2013 በግብጽ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ሃገሪቱ ከአፍሪካ ህብረት እንድትወጣ በመደረጉ የዚምባብዌ ጦርም ተመሳሳይ ዕጣ እንዳይደርሰው በመስጋት መፈንቅለ መንግሥት አለመሆኑን በማስተባበል ላይ ነው።

ድራማው ምን ይመስላል?

ከቀናት ውጥረት እና ሽኩቻ በኋላ ጦሩ የሃገሪቱን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሆነውን ዜድ ቢ ሲን ማክሰኞ በቁጥጥር ስር አዋለ።

የጦሩ አባል ሆኑት ሜጀር ጄነራል ሲቡሲሶ ሞዮ በቴሌቭዥን ቀርበው ዒላማቸው በሙጋቤ ዙሪያ በሚገኙ "ወንጀለኞች" ላይ መሆኑን አስታውቀው ነበር።

"ይህ ጦሩ የመግሥትን ስልጣን የተቆጣጠረበት አይደለም" ብለዋል።

ሜጀር ጄነራል ሞዮ ሙጋቤና ቤተሰቦቻቸው "በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እና ደህንነታቸውም እንደሚጠበቅ አረጋግጠዋል።"

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የዚምባብዌ ጦር ጄነራል ኮንስታንቲኖ ቺዌጋ (በስተግራ) ከስልጣን የተባረሩት የኤመርሰን ምናንጋግዋ ወዳጅ ናቸው
Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤና ኤመርሰን ምናንጋግዋ

ጦሩን ማን እንደሚመራ እሰካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ከመግለጫው በኋላ የጦሩ መኪኖች በሃራሬ ጎዳናዎች ላይ የተስተዋሉ ሲሆን ፕሬዝዳንት ሙጋቤና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በሚኖሩበት ሰሜናዊ የከተማዋ ክፍል ተኩስ ተሰምቷል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ጽህፈት ቤት "ፕሬዝዳንት ዙማ ዛሬ ከፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ጋር ተነጋግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ከቤታቸው እንዳይወጡ እንደተደረጉ ቢገልጹም በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛሉ" ብሏል።

ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤና ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ የት እንዳሉ በትክክል የማይታወቅ ሲሆን የተለያዩ ሪፖርቶች ግሬስ ሙጋቤ ናሚቢያ ገብተዋል ቢሉም የናሚቢያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ግን ግሬስ ሙጋቤ ናሚቢያ የሉም ሲሉ ተናግረዋል።

እንዴት እዚህ ተደረሰ?

በግሬስ ሙጋቤና ከስልጣን ተባረው የነበሩት ምክትል ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ መካከል ያለው ልዩነት ገዢው ዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲንም ለሁለት ከፍሎታል። ምናንጋግዋ ከስልጣን እንዲወርዱ ግሬስ ከጠየቁ በኋላ ከምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው ተነስተዋል።

ሰኞ ዕለትም የጦሩ ኃላፊ ጄነራል ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ የፓርቲውን መከፋፈል ለማስቆም ጦሩ ጣልቃ ይገባል ብለው ነበር።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ፕሬዝዳንት ሙጋቤና ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ

ጄነራሉ የምናንጋግዋ የቅርብ ወዳጅ ሲሆኑ እ.አ.አ በ1970ዎቹ በተካሄደውና የነጮችን አገዛዝ በገረሰሰውም ጦርነት ተሳትፈዋል።

የሙጋቤ ደጋፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የዛኑ ፒ ኤፍ ወጣት ክንፍ መሪ ኩዲዛይ ቺፓንጋ ጦሩ በማዘዣው መቆየት አለበት ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

እንደ ዜድ ቢ ሲ ዘገባ ከሆነ ቺፓጋ "ወጣቶች ነን። ጥፋት እንፈጽማለን" በማለት ጄነራል ቺዌንጋንና ሌሎች ከፍተኛ የጦር አመራሮችን ይቅርታ ጠይቋል።