ሳይድ ሃሪሪ፡ በፈረንሳይ ጥገኝነት ሳይሆን ቆይታ ለማድረግ ነው

Posters depicting Saad Hariri seen in Beirut, Lebanon, November 14, 2017 Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ የሳይድ ሃሪሪን ምስሎች የያዙ ፖስተሮች በሊባኖስ ርዕሰ መዲና ቤሩት ተሰቅለዋል

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሊባኖሱን ጠቅላይ ሚንስትር ሳይድ ሃሪሪና ቤተሰባቸውን ወደ ፈረንሳይ የጋበዙ ሲሆን ሳይድ ሃሪሪ የፖለቲካ ጥገኝነት እያቀረቡ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

የፈረንሳይ ባለስልጣናት እንዳሉት ሳይድ ሃሪሪ በመጪዎቹ "ቀናት ውስጥ'" ፈረንሳይ ይደርሳሉ።

ሳይድ ሃሪሪ ለጉብኝት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ካቀኑ በኋላ ነው ሳይጠበቁ ከስራ መልቃቀቸውን ያስታወቁት። በዚህም በሊባኖስ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ተፈጥሯል።

በአካባቢው ተቀናቃኟ የሆነችውን የኢራንን ተጽእኖ ለመቀልበስ ያለፍላጎታቸው ይዛቸዋለች እንዲሁም ከስልጣን እንዲለቁ አስገድዳቸዋለች በሚል የሚቀርብባትን ክስ ሳዑዲ ዓረቢያ ታስተባብላለች።

ባለፈው ረቡዕ የሊባኖሱ ፕሬዝዳንት ሚሼል አውን ጠቅላይ ሚንስትር ሳይድ ሃሪሪ ስለመመለሳቸው "ምንም ማረጋገጫ የለም" በሚል በይፋ ሳዑዲ ዓረቢያን ተችተዋል።

ሳይድ ሃሪሪ በበኩላቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና በቅርቡ ወደ ሊባኖስ እንደሚመለሱ አስታውቀዋል።

ጀርመንን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት ማክሮን "ለጥቂት ቀናት" የሚደረገው የፈረንሳይ ጉብኝት ከሳይድ ሃሪሪ እና ከሳዑዲው ልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማን ጋር በተደረገ የስልክ ውይይት ከመግባባት የተደረሰበት ነው ብለዋል።

ጥያቄው ጥገኝነትን ስለማካተቱ የተጠየቁት ማክሮን "በጭራሽ አይደለም። ሊባኖስ የተረጋጋች እንደምትሆን ተስፋ አለኝ። የፖለቲካ ምርጫው በህገ-መንግሥቱ መሠረት ይሆናል" ብለዋል።

Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ሳይድ ሃሪሪ እና ኢማኑኤል ማርኮን ባለፈው መስከረም ፈረንሳይ ውስጥ ተወያይተው ነበር

"ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ጠንካራ ሊባኖስ እንድትኖር እንፈልጋለን። በነጻነት ምርጫቸውን የሚያከናውኑ እና የሚናገሩ መሪዎችን እንፈልጋለን" ሲሉ ገልጸዋል።

የጉብኝቱ ጉዳይ የመጣው የፈረንሳዩ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኢቭ ለ ድሪዮን በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር ሳዑዲ አረቢያን ከጎበኙ በኋላ ነው።

ፕሬዝዳንት አውን በትዊተር ገጻቸው ሃሪሪ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት "ተይዘው ታስረዋል" ብለዋል።

"ከሃገር ውጭ በሚደረግ መልቀቂያ ጥያቄ ላይ ምንም ውሳኔ አይሰጥም። ወደ ሊባኖስ ተመልሶ መልቀቂያውን ማስገባት ወይም ውሳኔውን መቀየር፤ ስለጉዳዩ ምክንያት ማቅረብና ችግሮች እንዴት እንደሚፈቱ መነጋገር ያስፈልጋል" ሲሉ ገልጸዋል።

"በድጋሚ ማረጋገጥ የምፈልገውና የምገልጸው ጉዳይ ደህና መሆኔንና በገባሁት ቃል መሠረት ወደምወዳት ሊባኖስ እንደምምለስ ነው" ሲሉ ሃሪሪ ምላሻቸውን በትዊተር ሰጥተዋል።

የሃሪሪ ፓርቲ የሆነው የፊውቸር ሙቭመንት አባል ለሬውተርስ አንደገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩና ቤተሰባቸው በቁጥጥር ስር አልዋሉም።

ሃሪሪ ለህይወታቸው በመፍራት ከስልጣናቸው ለመልቀቅ መወሰናቸውን ከሳዑዲ ዓረቢያ ርዕሰ መዲና ሪያድ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ኢራን በአካባቢው ላይ "አለመረጋጋት፣ ጥፋት እና ውድመት" ለማስከተል እየተንቀሳቀሰች ነው በሚልም ከሰዋል።

የሃሪሪ አባት የሆኑት የቀድሞው የሊባኖስ ጠቅላይ ሚንስትር ራፊክ ሃራሪ በአጥፍቶ ጠፊ ቤሩት ውስጥ እ.አ.አ በ2005 ነበር የተገደሉት።

ከግድያው ጋር በተያያዘ በኢራን የሚደገፈው የሂዝቦላህ አባላት በሌሉበት ጉዳያቸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚደገፈው ዘ ሄግ ታይቷል።

ተያያዥ ርዕሶች