ህዳር ሲታጠን፡ ቆሻሻን ማስወገድ ወይስ አየርን መበከል?

Image copyright Facebook
አጭር የምስል መግለጫ ህዳር 12 2010 አዲስ አበባ

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በየዓመቱ ህዳር 12 ቆሻሻን ሰብስቦ በየደጁ ማቃጠል የተለመደ ተግባር ነው። የልማዱም አጀማመር ወደ ኋላ አንድ ክፍለ-ዘመንንም ይጓዛል።

ለመሆኑ እንዴት ተጀመረ?

በ1911 በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በአውሮፓ ለሚሊዮኖች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት የሆነው 'ስፓኒሽ ፍሉ' የተባለ የኢንፍሉዌንዛ በሽታ ወረርሽኝ ተከስቶ ነበር።

ይህ በሽታም በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ለበርካቶች ሞት ምክንያት ሲሆን ለበሽታውም የተለያዩ ስያሜዎች ተሰጥተውት ነበር። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁር የሆኑት አቶ አበባው አያሌው የበሽታውን አመጣጥ አስመልክቶም የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መንገድ ስራ በጀመረበት ወቅት በሽታው በመነሳቱ ምክንያት ባቡሩ ያመጣው በሽታ ነው በማለት "የባቡር በሽታ" ይባል እንደነበር ይናገራሉ። በተጨማሪም የተከሰተበትን ወር ተከትሎም "የህዳር በሽታ" ተብሎ መጠራት እንደጀመረም ይናገራሉ።

በሽታው በህዳር ወር 1911 ዓ.ም በአዲስ አበባ ብቻ ከ6 ሺ ሰው በላይ መግደሉንም ጥናቶች ያሳያሉ። ይህንንም ተከትሎ በጀርመን ሀኪሞች ምክክር ህዝቡ ቆሻሻ ከቤታቸው አውጥተው እንዲያቃጥሉ በአዋጅ መለፈፉን አቶ አበባው ይናገራሉ።

"ይህም የበሽታው መንስዔ ቆሻሻ እንደሆነ በመታመኑ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በሽታው በአየር ይተላለፋል ተብሎ ስለታመነም አየሩን እንደማጠን ይቆጥሩታል" ይላሉ።

ከጊዜ በኋላም አየሩ ስለታጠነ ነው በሽታው የጠፋው ተብሎ በየዓመቱ ቆሻሻን ማቃጠልን ህዳር ሲታጠን የሚል ስያሜ ማግኘቱም ከዚህ ተነስቶ መሆኑን ያብራራሉ።

Image copyright Facebook
አጭር የምስል መግለጫ ህዳር 12 2010 አዲስ አበባ

ምንም እንኳን ቆሻሻን ማቃጠል ለአካባቢ ንፅህና ጥሩ ቢሆንም ለአየር ንብረት አሉታዊ አስተዋፅኦ ስላላው ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

"የሚቃጠሉት ቁሳቁሶች በተለይም ፕላስቲክና የባትሪ ድንጋዮች ሃይድሮፍሎሮ ካርበን፣ ሜቴንና ካርበንዳይሞኖክሳይድ የተባሉ ንጥረ-ነገሮችን በውስጣቸው ስለሚይዙ ለአየር ብክለት የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው" ይላሉ።

በዓለም የአግሮ ፎረስትሪ (የግብርናና ደን ማዕከል) ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ለሊሳ ዱጉማ በበኩላቸው የሚቃጠለው ቆሻሻ መጠን እና የሚቃጠልበት አካባቢ ወሳኝ ነውም ይላሉ።

"ገጠር አካባቢ ከሆነ የሚቃጠለው አብዛኘው የተፈጥሮ ተዋፅኦ ስለሆነ ብዙም ችግር ላይኖረው ይችላል። ከተማ አካባቢ ግን የተለያዩ በኬሚካል የተሞሉ ንጥረ-ነገሮች ስለሆኑ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ" በማለት ዶክተር ለሊሳ ይገልፃሉ።