የአርጀንቲና መርከብ ችግር እንደደረሰበት ደውሎ አሳውቆ ነበር

the Argentine Navy on 17 November 2017 Image copyright EPA

ከዕለተ ረቡዕ ጀምሮ ደብዛው የጠፋው የአርጀንቲና የባሕር ኃይል መርከብ ሠራተኞች መካኒካዊ ችግር እንደገጠማቸው በመጨረሻ ግንኙታቸው አሳውቀው ነበር ተባለ።

የአርጀንቲና ባሕር ኃይል ንብረት የሆነው ሳን ሁዋን መርከብ 44 ሠራተኞችን እንዳሳፈረ ከአርጀንቲና ወደብ 430 ኪሎ ሜትር አካባቢ እንደጠፋ ቀርቷል።

የሃገሪቱ አየር ኃይል ሰኞ ዕለት በአሰሳው ወቅት ተሰምቶ የነበረው ድምፅ ከጠፋው መርከብ የወጣ እንዳልሆነ አስታውቋል። አሁድ ዕለትም መሰል ምልክት ታይቶ የነበረ ቢሆንም ከጠፋው መርከብ እንዳልሆነ ግን ለማወቅ ተችሏል።

ከጠፉት 44 ሰዎች መካከል የአንዱ ወንድም የሆነ ግለሰብ ለመጨረሻ ጊዜ ከወንድሙ ጋር በነበረው ግንኙነት መርከቡ ከባትሪ ጋር በተያያዘ ችግር እንደገጠመው መስማቱን ለሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አሳውቋል።

ነገር ግን የአርጅንቲና ባሕር ኃይል ካፕቴይን ጋሌዚ እንደሚሉት መካኒካዊ ችግር ሁሌም የሚፈጠር እንጂ አዲስ ነገር አይደለም፤ የሚያደርሰው አደጋም እጅግ ዝቅተኛ ነው። መርከቡ እክል እንዳጋጠመው ካሳወቀ በኋላም ቢሆን ወደ መቀመጫ ወደቡ በሰላም እየተመለሰ እንደበረም ነው ካፕቴኑ የሚናገሩት።

መርከቡን ፍለጋ ሰፊ የሆነ እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን እስካሁን የተገኙ ሰባት ምልክቶች ከጠፋው መርከብ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ማወቅም ተችሏል።

ከአሜሪካ ወደ አርጀንቲና ፍለጋውን ለማገዝ የመጣው ዘመናዊ የውሃ ውስጥ አሳሽ መሣሪያም ፍለጋው ቢቀላቀልም ከባድ የአየር ሁኔታ አሰሳውን እንዳከበደው እየተነገረ ይገኛል።

መርከቡ ከደቡብ አሜሪካ ደቡባዊ ጫፍ የተሰጠውን ተልዕኮ ጨርሶ በአርጀንቲና ርዕሰ-መዲና ቦነስ አይረስ ወደሚገኘው መቀመጫው እየተመለስ ነበር።