ጃማይካዊው የአማርኛ ቋንቋ አስተማሪ

ስቲቨን ዶኖቫን ልዊስ
አጭር የምስል መግለጫ ስቲቨን ዶኖቫን ልዊስ፡ ጀማይካዊው የአማርኛ ቋንቋ አስተማሪ

ስቲቨን ዶኖቫን ልዊስ እባላለሁ። የጃማይካ ዋና ከተማ ከሆነችው ኪንግስተን ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ነበር።

ወደዚህ ካመጡኝ ጉዳዮች መካከል አንዱ እምነቴ ነው። ከተመረጡት ከአብርሃም ልጆች መካከል አንዱ በሆኑት በንጉስ ኃይለሥላሴ ውስጥ አንድ ነገር በማየቴ ነው።

ኃይለሥላሴ ከአብርሃም ልጆች መካከል ናቸው። የእግዚያብሔር ልጆች እንደማለት ነው።

እኛ ኢትዮጵያዊያን ሁላችንም የአብርሃም ልጆች ነን። እኛ ጃማይካዊያንም የአብርሃም ልጆች መሆናችንን እናውቃለን።

ስለዚህም ኃይለሥላሴ ወደ ጀማይካ ሲመጡና 'ከይሁዳ ነገድ መካከል ነኝ' ሲሉ ይህንን ተቀብለናቸዋል። ኃይለሥላሴን እንደ ፈጣሪ አናመልካቸውም። አምላክ መንፈስ ስለሆነ። ፈጣሪ ዳዊትን እውነተኛ ንጉስ እንዲሆን ነው የመረጠው። ይህም ክርስቶስ በንጉስ አምሳያ ምድር ላይ አለ ማለት ነው። ዳዊት ማለት ይህ ነው።

ከእምነቴ በተጨማሪ ወደ ኢትዮጵያ ያመጣኝ ሌለው ነገር አማርኛ ቋንቋ ለመማር ያለኝ ጥልቅ ፍላጎት ነው። ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ቋንቋውን የመማር ዕድል እንደማገኝ ትልቅ ተስፋ ነበረኝ። ቋንቋውን አቀላጥፌ ለመናገር ብዙ ጥረት እያደረኩ ነው። በቅድሚያ አዲስ አበባ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ ባህር ዳር ሄጄ ተምሬያለሁ።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ራስ-ተፈሪያውያን አማርኛ ቋንቋን መማር እንዳለባቸው ይሰማኛል። ይህን ለመደገፍ የአማርኛን ቋንቋ መማር ለሚፈልጉ ፊደላቱን እያስቆጠርኩ ነው።

እስካሁን ድረስ አስራ አምስት ተማሪዎችን አስተምሬያለሁ። አማርኛ ከእንግሊዝኛ በበለጠ ለሰው የቀረበ ቋንቋ ነው፤ ለምሳሌ ከወንድ ጋር ስታወሩ፥ ዓረፍተ ነገሩ ወንድን የሚያመለክት ነው። ከሴት ጋር ስታዋሩም እንደዚያው። ቋንቋው ለትልቅ ሰዎችም ክብር እንድንሰጥ ያስችለናል። በእነዚህ ምክንያቶች አማርኛ ብልህ ቋንቋ እንደሆነ ይሰማኛል። ወንድ እና ሴት አብረው ቆመው ቢሆንና ለአንዳቸው ብቻ ሰላምታ መስጠት ቢያስፈልግ ያንን ማድረግ ይቻላል። ለሁለቱም ሰላምታ ማቅረብ ካስፈለገም እንደዚያው ማድረግ ያስችላል።

ለእኔ አማርኛን መማር ወደሰው ልብ በዚያውም ወደአምላክ እንደመቅረብ ነው። ግዕዝም በጣም አስፈላጊ እንደሆነ አውቃለሁ። ምናልባትም ወደፊት ግዕዝ መማሬ አይቀርም።

እንግሊዝኛ ግን እንደዚያ አይደለም። በእንግሊዝኛ 'ሰላም' ማለት በቃ 'ሰላም' ብቻ ነው።

አጭር የምስል መግለጫ ስቲቨን ዶኖቫን ልዊስ፡ ጀማይካዊው የአማርኛ ቋንቋ አስተማሪ

የሀገሬ ይፋዊ የሥራ ቋንቋ እንግሊዝኛ ቢሆንም ለኔ ግን እንግሊዝኛ የኔ ቋንቋ እንደሆነ አይሰማኝም። ለእኔ እንግሊዝኛ የአባቶቼ ቋንቋ አይደለም። አባቶቼ አፍሪካዊያን ናቸው።

እንግሊዝኛ የሚነገርበት ሀገር ረጅም ዓመት ስለኖርኩ የማንነቴን ቋንቋ አጥቼ ነበር። አሁን ግን ተመልሼ መጥቼ አማርኛ ተማርኩ። አማርኛ በመማሬም በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ምክንያቱም ቋንቋውን ማወቄ ኃይማኖቴን የበለጠ እንድገነዘበው ይረዳኛል።

አንድ ኢትዮጵያዊ አሁን ወደጃማይካ ቢሄድ ስለሥራ ምንም ጭንቀት አይገባውም፤ አስተማሪ መሆን ብቻ ይበቃዋል። አማርኛ የመማር ፍላጎት ያላቸው በጣም ብዙ ሰዎች አሉ።

ፊደል ከማስቆጠር በተጨማሪ ጨርቅን በመጠቀም የተለያዩ ጌጣጌጦችን እሰራለሁ። ለሴቶች የሚሆኑ ልብሶችን፣ የፀጉር ማስያዣ እና የአንገት ጌጦችን እሰራለሁ።

ከአሁን በኋላ ወደ ጃማይካ ተመልሶ የመሄድ ፍላጎት የለኝም። ይልቁንም ተጨማሪ ጃማይካዊያን ወደዚህ እንዲመጡ ነው የምፈልገው።

ተያያዥ ርዕሶች