ህንዳዊቷ ተማሪ ራሷን በማጥፋቷ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲውን አቃጠሉ

በህንድ ዩኒቨርስቲ የተነሳ የእሳት ቃጠሎ

ፈተና ስታጭበረብር የተገኘት ተማሪ ራሷን በመግደሏ በህንድ ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቷል።

ቼናይ በሚገኘው የሳትሀይብሃማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የመማሪያ ወንበሮችን ትናንት ምሽት ላይ እንዳቃጠሉ የሃገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ተቃውሟቸውን እየገለፁ ያሉ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲው መምህራንንና አስተዳደሩን ተማሪዋን በማሸማቀቅ ወንጅለዋል።

የ18 ዓመት ዕድሜ የነበራት ይህቺ ተማሪ ፈተና ስታጭበረብር ተገኝታለች በሚል ከፈተና አዳራሽ የተባረረች ሲሆን ወዲያውም ክፍሏ ውስጥ ገብታ ራሷን አንቃ ገድላለች።

ዘ ታይምስ ኦፍ ኢንዲያ የተባለው የሀገሪቱ ሚዲያ የዩኒቨርስቲ ኃላፊዎችን አናግረው እንደዘገቡት ሬሳዋም በመንታ እህቷ ተገኝቷል።

የሞቷም ዜና ሲሰማም ተማሪዎቹ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፋቸውን የጀመሩት።

ምንጣፎችና ወንበሮችም በእሳት እንደተቀጣጠሉም በትዊተር ድረ-ገፅ ላይ የወጡ ቪዲዮዎችና ፎቶዎች ያሳያሉ።

"የአንደኛ አመት ወንድ ተማሪዎች የሚያድሩበት ዶርሚተሪ ውስጥ ዕቃዎች አቃጥለዋል። ዛፎችንም አቃጠሉ። ህንፃዎቹ በቃጠሎው የተጎዱ አይመስለኝም። ወደ አምስት ሰዓትም አካባቢ በኮሌጁ በር አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ህዝብም ተሰብስቦ ነበር" በማለት አንድ ተማሪ ለህንዱ ሚዲያ ዘ ኒውስ ሚነት ተናግሯል።

ፖሊስ ሀሙስ ጥዋት ከተጠራ በኋላ ተቃውሞውም ተረጋግቷል።

ተያያዥ ርዕሶች