የአየር ብክለት በከተሞች ለሚደረጉ ማራቶኖች ስጋት ነው?

አዲስ አበባ Image copyright Getty Images

ባለፈው ሳምንት በደልሂ በተካሄደው ማራቶን ውድድር ላይ የፊት ጭንብል አድርገው የሚሮጡ አትሌቶች ምስል በብዙ ከተሞች ያለው የአየር ብክለት ምን ያህል አደጋ እንደደቀነ የሚያሳይ ነው።

የአየሩ ብክለት መርዛማ ደረጃ ደርሷል በተባለለትና ትምህርት ቤቶች እስኪዘጉ ምክንያት በሆነው በዚህ የአየር ብክለት ምክንያት ውድድሩ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ አንዳንድ የህክምና ባለሙያዎች ጠይቀው ነበር።

ሆኖም ውድድሩ በተካሄደበት ወቅት የነበረው አየር 'አደገኛ' ከሚል ደረጃ ወርዶ 'ለጤና የማይስማማ' በሚል ደረጃ በተቀመጠበት ወቅት ነው የተካሄደው። በውድድሩ ብርሃኑ ለገሰ በወንዶች አልማዝ አያና ደግሞ በሴቶች ቀዳሚ ሆነው መግባት ችለዋል።

ከውድድሩ በፊት ብርሃኑ አትሌቶቹ 'ፈርተው እንደነበር' ገልጾ በውድድሩ ቀን የነበረው ሁኔታ ግን 'መጥፎ አለመሆኑን' ጠቅሷል።

በከተሞች በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ አትሌቶችም ሆኑ ሌሎች ተሳታፊዎች የአየር ብክለት ሊያሰጋቸው ይገባል?

ምንም አዲስ ነገር የለም

የአየር ብክለት ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በስፖርታዊ ወድድሮች ላይ ስጋት እየፈጠሩ ነው።

እ.አ.አ በ1984 የተካሄደው የሎስ አንጀለስ ኦሎምፒክ በአየር ብክለት ምክንያት ሌላ ጊዜ መካሄድ ነበረበት የሚሉ ነበሩ። የቻይና ባለስልጣናት ፋብሪካዎችን ዘግተው መኪኖችን ቢያግዱም፤ የ2008ቱ የቤጂንግ ኦሎምፒክ ደግሞ በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ ብክለት ያጋጠመበት ነበር።

በነዋሪዎች ቁጥር መጨመር እና አየርን በሚበክሉ የተለያዩ ምክንያቶች በብዙ ከተሞች ያለው አየር እየተበከለ ይገኛል።

አትሌቶች ለአነስተኛ ጊዜ በጣም በተበከለ አየር ውስጥ ቢወዳደሩ በጤናቸው ላይ የሚያስከትለው የረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ከድምዳሜ አልተደረሰም።

ዋናው ችግር በተበከለው አየር ውስጥ ለሚኖሩት ዜጎችነው።

Image copyright Getty Images

እንደዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ከሆነ በአየር ብክለት ምክንያት በየዓመቱ ሶስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ። እንቅስቃሴ ማድረግ የምንስበውን የአየር መጠን ከፍ የሚያደርገው ሲሆን ከፍተኛ ብክለት ባለባችው አካባቢዎች ደግሞ ይህ ችግር የበዛ ይሆናል።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአየር ብክለት ሁኔታ 'መካከለኛ' የሚባል ነው።

በኢትዮጵያ ስላለው የአየር ብክለት ያለው ሳይንሳዊ መረጃ ትንሽ ነው። ሆኖም ተመራማሪዎች በምስራቅ አፍሪካ ለሚከሰተው ያለዕድሜ ሞት ትልቅ ምክንያት ነው ይላሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በምስራቅ አፍሪካ ስላለው የአየር ብክለት በሚደረገው ጥናት ውስጥ አዲስ አበባ ተካታለች። ጥናቱ እ.አ.አ ከ2015 እስከ 2030 ባለው ጊዜ የከተማዋ ነዋሪ ቁጥር በ80 በመቶ ስለሚያድግ መንግሥት እርምጃ መውሰድ እንደሚገባው ለማሳሳብ ነው።

ብዙ ሰዎች ምግባቸውን ለማብሰል ከሰል የሚጠቀሙ ሲሆን ቆሻሻ በየመንገዱ ከመቃጠሉም በላይ የመኪኖች ቁጥር እያደገ ነው።

አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ያለው የክትትል ቡድን ባለፈው አርብ የከተማዋን የአየር ሁኔታ 'መካከለኛ' ሲል አስቀምጧል። በዚህ ደረጃ መሠረት ህጻናት፣ ታዳጊዎችና የመተንፈሻ ችግር ያለባቸው ሰዎች ለረዥም ሰዓት ከቤት ውጭ ማሳለፍ አይገባቸውም።

የልምምድ ቦታዎች

ብዙ ታዋቂ እና ጀማሪ አትሌቶች ባለው የልምምድ መሠረተ ልማት ምክንያት መሠረታቸውን በአዲስ አበባ በማድረግ እየተለማመዱ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ኃላፊ ሃይሌ ገብረስላሴ ችግሩ መኖሩን ገልጾ ጎጂ መሆኑን ይጠቅሳል።

የቀድሞው የኦሎምፒክ ሻምፒዮን በቅርቡ አትሌቶች በአየር ብክለት ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከአዲስ አበባ ውጭ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል።

ያለፈው ዓመት የቦስተን ማራቶን አሸናፊው ለሚ ብርሃኑ ግን የብክለቱ ችግር አነስተኛ ነው ሲል ይገልጻል።

"ስለ አየር ብክለት አናውቅም። አሰልጣኞቻችንም ስለዚህ ጉዳይ አይነግሩንም።"

Image copyright Getty Images

ዋናው ትኩረት በእርጥበት፣ የሙቀት መጠን፣ ከፍታ እና በተለያዩ የአየር ንብረቶች በመወዳደር ላይ እንጂ በሚወዳደሩበት ቦታ ስላለው የአየር ብክለት ትኩረት አይደረግም ይላል።

የቻይናው ዢያሚን እና የዱባይ ማራቶኖች አሸናፊው ለሚ በአየር ብክለት ምክንያት እስካሁን ምንም ጉዳት እንዳልደረሰበት አስታውቋል።

የማራቶን አሰልጣኝ የሆኑት ሃጂ አዴሎ በበኩላቸው ጉዳዩን ለአትሌቶች እንደሚያሳውቁ እና የበለጠ እየተረዱት መሆኑንም ይገልጻሉ።

"በትልልቅ የውጭ ከተሞች ካለው የአየር ብክለት በተጨማሪ በአዲስ አበባም ተመሳሳይ ነገር አለ። አትሌቶቹ የሚስቡት አየር የተበከለ ሊሆን ይችላል። በጫካ ውስጥ ሲለማመዱ የሚያገኙት ንጹህ አየር ላይሆን ይችላል" ብለዋል።

አነስተኛ ስጋት

በአዲስ አበባ የተደረገው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር አዘጋጆች ግን የአየር ብክለት አያሳስበንም ይላሉ።

በአስር ኪሎ ሜትሩ ውድድር ላይ 44 ሺህ ሰዎች ተሳትፈዋል።

የውድድሩ ዳይሬክተር ኤርሚያስ አየለ በከተማው አንዳንድ ጊዜ ጥሩ ያልሆነ አየር እንደሚኖር ጠቁመው ችግሩ እንደማያሳስባቸው ገልጸዋል።

"ውድድሩ መኪኖች በብዛት በማይኖሩበት ወቅት እሑድ ተካሂደዋል። የውድድሩ ቦታ ሙሉ ለሙሉ ለትራፊክ ዝግ ነው። በዚህ ምክንያት የአየር ብክለት ስጋት አይሆንም" ብለዋል።