በኢንዶኔዥያ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ስጋት ከፍተኛ ሆኗል

በባሊ በተከሰተው የእሳተ ገሞራ ከተራራው ጫፍ ጭስ እየተትጎለጎለ ሲወጣ ይታያል።
አጭር የምስል መግለጫ በአጉንጉ ተራራ አቅራቢያ ይኖሩ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእሳተገሞራው ምክንያት መኖሪያቸውን እየለቀቁ መሄድ ጀምረዋል።

የኢንዶኔዢያ ባለስልጣናት በደሴቲቱ የአደጋ ስጋቱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ አሸጋግረውታል።

የቱሪስት መዳረሻ በሆነችው በዚህች ደሴት የአየር መንገዱ የተዘጋ ሲሆን በዚህም የተነሳ በርካታ ጎብኝዎች ጉዟቸው ተስተጓጉሏል።

ጥቁር ጭስ ከተራራው ጫፍ 3400 ከፍታ በላይ እየተምዘገዘገ ሲወጣ ይታያል።

የሃገሪቱ የብሄራዊ የአደጋ መቆጣጠር እንዳለው ከሆነ ፍንዳታ ከ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተሰምቷል።

የባሊ ዋነኛ መዝናኛ የሆኑት ኩታ እና ሴሚንያክ ከእሳተ ገሞራው በ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ናቸው።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ የሃገሪቱ ባለስልጣናት የእሳተ ገሞራው "በተከታታይ አመድ መትፋት ጀምሯል" ብለዋል።

የአደጋ ማስጠንቀቂያው ወደ ደረጃ አራት ከፍ ያለው በሃገሪቱ ሰአት አቆጣጠር ከ 6፡00 ሰአት ጀምሮ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ተጨባጭ የሆነ እና ህይወትን ጉዳት ላይ የሚጥል ቀውስ ሊኖር ስለሚችል ነው ተብሏል።

ሰኞ እለት የአደጋ መከላከል ኤጀንሲው እሳተ ገሞራው 'በፍንዳታ የታጀበ አመድ' መትፋት ቀጥሏል ፤ ይህም 'በፍንዳታ' የታጀበና 'አነስተኛ ድምፅ' የነበረው ነው ብለዋል።

በፌስ ቡክ የማህበራዊ ድረ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መግለጫ በምሽት የእሳት ፍላፃ መታየት ጀምሯል። ይህ ደግሞ ቀጥሎ ከባድ ፍንዳታ አይቀሬ እንደሆነ አመላካች ነው ብለዋል።

ባለስልጣናት ለነዋሪዎች ጭምብል እያከፋፈሉ ሲሆን በ10 ኪሎ ሜትር ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ትተው እንዲወጡ እያደረጉ ይገኛሉ።

የአደጋ መከላከል ኤጀንሲ ቃል አቀባይ የሆኑት ሱቶፖ ፑርዎ ኑግሮሆ በተጨማሪም በሚኖረው ከባድ ዝናብ የተነሳ ስለሚፈጠረው ቀዝቃዛ ላቫ በማስጠንቀቅ ነዋሪዎች ከወንዞች አካባቢ እንዲርቁ አስጠንቅቀዋል።

እሳተ ገሞራው የዛሬ 50 አመት ከፈነዳ በኋላ ባለፈው ሳምንት ነበር ጭስ መትፋት የጀመረው። ከዛ ጊዜ ጀምሮ የነጉድጓድ ድምፅ መሰማት ቀጥሏል።

ቅዳሜ እለት ባለስልጣናት እና የእሳተ ገሞራ ጥናት ባለሙያዎች ቀላጭ አለት በተራራው ዙሪያ መገኘቱን አረጋግጠዋል።

የአዴላየድ ዩኒቨርስቲ ጂኦሎጂስት የሆኑት ማርክ ቲንጌይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ የአጉንግ ተራራ አሁን ወደ ቀላጭ አለት ፍንዳታ ደረጃ የተሸጋገረ ሲሆን ፍም ላቫ በእሳተገሞራው አፍ ዙሪያ መታየት ጀምሯል።

ነገር ግን ሁኔታው በምን ያህል ደረጃ እያደገ እንደሚሄድ መተንበይ አስቸጋሪ ነው።

' ይህ ፍንዳታ ትልቅ፥ቀጣይ እና አስፈሪ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ደግሞ በንፅፅር በጊዜ ሂደት አነስተኛ ፍንዳታ ሊሆን ይችላል።'

የሃገሪቱ ባለስልጣናት እንዳሉት የባሊ ንጉራህ ራይ አየር መንገድ እስከ ማክሰኞ ጥዋት ድረስ ዝግ ስለሆነ እስከዛ ድረስ ማንኛውም አይነት በረራዎች መሰረዛቸውን አሳውቀዋል።

በሌላኛው ደሴት የሚገኘው ሎምቦክ ለአጭር ጊዜ ከተዘጋ በሗላ ሰኞ ጥዋት በድጋሚ ተከፍቷል።

ባለስልጣናት የሎምቦክ ከተማ በሆነችው ማታራም የአመድ ዝናብ መዝነቡን ተናግረዋል።

በቅርቡ ወራት ወደ 14000 ያህል ሰዎች ከተፈናቀሉ በሗላ 25000 የሚሆኑ ሰዎች በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ይገኛሉ።

ባለስልጣናት ለመጀመሪያ ጊዜ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ሊኖር እንደሚችል የማስጠንቀቂያ መልእክት ያስተላለፉት እና ማስጠንቀቂያውን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከፍ ያደረጉት በመስከረም ወር ከፍተኛ የሆነ የእሳተገሞራ እንቅስቃሴ መኖሩ ከታወቀ በኋላ ነው፤ ይህም ነዋሪዎች ከቦታው እንዲለቁ አድርጓል።

አንዳንድ የደሴቲቱ ነዋሪዎች ግን በጥቅምት ወር የአደጋ ማስጠንቀቂያ ደረጃው ዝቅ ከተደረገ በሗላ ወደ መኖሪያ ስፍራቸው መመለስ ጀምረዋል።

ኢንዶኔዢያ የምትገኘው በፓስፊክ የእሳት ቀለበት እየተባለ በሚታወቀው ክልል ውስጥ ነው።

ይህ ስፍራ 130 ንቁ እሳተ ገሞራዎች የሚገኙበት ነው።

የአጉንግ ተራራ ለመጨረሻ ጊዜ የፈነዳው በ1963 ሲሆን በወቅቱም ከ1000 ሰዎች በላይ ህይወታቸውን አጥተዋል።

ተያያዥ ርዕሶች