የደቡብ ሱዳን ስደተኞች የኡጋንዳን ምጣኔ ሃብት እያሳደጉ ነው

Refugee entrepreneur Penina cutting hair

"አዲስ ንግድ መጀመር እጅግ ከባድ ነው፤ ምክንያቱም መጀመሪያ ላይ ትርፍ ብዙ ስለማይገኝ" ትላለች አራት ልጆቿን ይዛ ከደቡብ ሱዳን ወደ ኡጋንዳ የተሰደደችው ፔኒና።

አዲስ ንግድ የመጀመር ትልቁ ፈተና መጀመሪያ ላይ ትርፋማ ያለመሆን ጉዳይ እንደሆነ እሙን።

ነገር ግን ከደቡብ ሱዳን ጦርነት ሸሽተው የመጡ ስደተኞች በተጠለሉባት ኡጋንዳ አዲስ ንግድ ሲጀምሩ ምን ያህል ሊከብዳቸው እንደሚችል ማሰቡ በራሱ ያዳግታል።

"ስደተኛ ሆኖ ገንዘብ ማግኘት በራሱ ከባድ ነው" በማለት ታክላለች ፔኒና

ፔኒና አንዲት ሴትና ልጆቿ ሲገደሉ ከተመለከተች በኋላ ባሏን ጥላ አራት ልጆቿን ይዛ ለመሰደድ ተገደደች።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ ገለፃ አሁን ላይ ኡጋንዳ ውስጥ ከሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደቡብ ሱዳናዊ ስደተኞች 85 በመቶ ያህሉ ሴቶችና ሕፃናት ናቸው።

ከኢትዮጵያና ኤርትራ ተሰደው ለብዙ ዘመናት በኡጋንዳ የቆዩ ስደተኞችም አሉ። ከኡጋንዳ መንግሥት፣ ከተባበሩት መንግሥታትና ከዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች የተወሰነ ድጋፍ ያገኛሉ።

በሣር የተወረሰ መሬት ከተሰጣቸው በኋላ እሱን አፅድተው መጠለያ መገንባት ከቻሉም ሰብል ማብቀል የስደተኞቹ ፋንታ ነው። አልፎም ከዝናብና ፀሐይ መከላከያ ላስቲክ፣ አንዳንድ የማብሰያ ዕቃዎችና የተወሰነ ምግብ ይሰጣቸዋል።

ነገር ግን ከዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የሚለገሰው ድጋፍ በመቀነሱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የምግብ አቅርቦት መቀነሱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ስደተኞች ይናገራሉ።

አሁን ላይ እየተለገሰላቸው ያለው ምግብ ለወር እንኳን እንደማይቆይ ነው የሚናገሩት።

በ1990ዎቹ መባቻ ላይ በደቡብና ሰሜን ሱዳን መካከል ግጭት በተቀሰቀሰ ወቅትም ወደ ኡጋንዳ ተሰዳ ነበር ፔኒና።

ኡጋንዳ ውስጥ እንዴት ሕይወቷን መግፋት እንዳለባት ከሌሎቹ በተሻለ ታውቃለች።

ሃገር ቤት እያለች የፀጉር ማሳመር ሥራ ትሰራ የነበረው ፔኒና በተጠለለችበት ሥፍራ የፁገር ማሳመሪያ ሱቅ ከፈተች።

ነገር ግን ንግዱ በጣም ቀዝቃዛ ነው ትላለች።

ገንዘብ መክፈል የማይችሉ ተገልጋዮች የተሰጣቸውን ምግብ ይሰጧታል።

እሷም በተራዋ ያንን ምግብ በመሸጥ ገንዘብ ታገኛለች። "ምን ማድረግ እችላለሁ? ሁኔታው በጣም ከባድ ነው" ትላለች።

ብዙም ሳይርቅ ደግሞ አንድ ወጣት በከሰል ተከቦ ይታያል። ስደተኞቹም ሆኑ ኡጋንዳውያን ከሰሉን ለምግብ ማብሰያነት ይጠቀሙታል።

"ንግድ በጣም እየጦፈ ነው" ይላል የ25 ዓመቱ ኡጋንዳዊ አብዱልካሪም አሊ።

አሩዋ ከተባለ ቦታ የመጣው አብዱልካሪም ደቡብ ሱዳናዊ ስደተኞች ያዘጋጁትን ከሰል በመግዛት ወደ ከተማ ወስዶ በትርፍ ይሸጣል።

"ከተማ ውስጥ ከሰል በጣም ውድ ነው። ስደተኞቹ ግን በርካሽ ዋጋ ይሸጡልኛል" ሲል ያስረዳል።

"አንዳንዶቹ ከተባበሩት መንግሥታት የተለገሳቸውን ቁሳቁስ ይሸጡልናል። እኛም እሱን ወስደን በአሪፍ ዋጋ እንሸጣለን" በማለት ያክላል።

"ነገር ግን ከተባበሩት መንግሥታት ለስደተኞች የተሰጠ ቁሳቁስ ስነግድ በፖሊስ ከተያዝኩ በጣም አደጋ ነው" ይላል "ቢሆንም አትራፊ ስለሆነ አላቆመውም" ሲል ይቋጫል።