የማንባብ ልምድን ለማዳበር የሚደረጉ ጥረቶች

ቤተ-መፃሕፍት Image copyright ARIS MESSINIS

በተፈጥሮ ሃብት የበለጸጉት ሃገራት ብቻ የአለም ፖለቲካንና ኢኮኖሚ የመቆጣጠር እና ተጽኖ የመፍጠር አቅም እንደነበራቸው የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው። በአሁኑ ግዜ ግን ያ ቀርቶ በእውቀት የተመሰረተ ኢኮኖሚ የገነቡ ሃገራት ዓለምን ሲያሽከረክሩ እንደሚስተዋሉ ሙሁራን ይገልጻሉ።

በዜጎቻቸው አእምሮ ላይ ትልቅ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ እና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ ተሳክቶላቸዋል የሚባሉት እነ እስራኤል፣ ጃፓን፣ ቻይና፣ ህንድ እና ግብጽ ተጠቃሽ መሆናቸውን ይነገራል።

ከዚህ በተጨማሪ የማንበብ ባህል ያዳበረ ማህበረሰብ ነገሮችን በሰከነ አኳኋን በመረዳት በምክንያታዊነትን እንዲላበስ ያግዘዋል የሚሉት በመቐለ ዩኒቨርስቲ የህብረተሰብ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ዜናዊ ዘሪሁን፤ ኢትዮጵያ ዜጎቻቸው ከማያነቡት ሃገራት ተርታ እንደምትገኝ ይናገራሉ።

ለመሆኑ የኢትዮጵያውያን የማንበብ ባህል ከምንድረስ ነው?

በአዲስ አበባ የህብረተሰቡ የማንበብ ባህል የሚያሳድግ የሬድዮ ፕሮግራም በማዘጋጀት የሚታወቀው የብራና ሬድዮ ዋና አዘጋጅ በፍቃዱ አባይ የኢትዮጵያውያን የማንበብ ባህል ከግዜ ወደ ግዜ እየቀነሰ መምጣቱን ይናገራል።

ላለፉት ስምንት ዓመታት ሰዎች የማንበብ ጠቀሜታ እንዲገነዘቡ የሚያስችሉ ዝግጅቶች መስራቱን የሚገልጸው በፍቃዱ፤ አዲሱ ትውልድ ለፈተና ይጠቅመኛል ያለዉን ከማንበብ ውጭ አጠቃላይ አስተሳሰቡን ለመቀየር የሚያስችሉትን መጽሃፍቶች ሲያነብ አይስተዋልም ይላል።

የህብረተሰቡ የማንበብ ባህል ለማሳደግ ምን እየተሰራ ነው?

እንደ አቶ በፍቃዱ ገለጻ በአዲስ አበባ ከሚያሰራጨው የሬድዮ ዝግጅት በተጨማሪ ከጀርመን ባህል ማዕከል ጋር በመተባበር በወር አንዴ የሚካሄደውን የማንበብ ቀን በማዘጋጀት ሰዎች ያላቸውን ዕውቀት እርስ በርሳቸው እንዲለዋወጡ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። በመድረኩ በአማካይ እስከ 150 ሰዎች እንደሚሳተፉም ገልጸዋል።

'የአንድን ማሕበረሰብ የማንበብ ባህል ሊዳብር የሚችለው በዋነኛነት ከቤተሰብ በመጀመር ነው። ቀጥሎ ወደ መምህራን እና ትምህርት ቤቶች እያለ ይቀጥላል'' የሚለውን አቶ በፍቃዱ የመንግሥት ሚናን 10ኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጠዋል።

ዩኤስ ኤይድ የኢትዮጵያ የማንበብ ባህል አስመልክቶ ባጠናው መሰረት ትግራይ ክልል በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧ ያሳሰባቸው አንዳንድ የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎችም ፌስቡክን ተጠቅመው መጽሓፍትን በማሰባሰብ ወደተለያዩ ትምህርት ቤቶች አድርሰዋል።

ለምሳሌ ከሃይማኖታዊ በዓላት ጋር በማያያዝ ፌስቡክ ላይ ሰዎች የቻሉትን መጽሃፍት እንዲለግሱ በማድረግ በሺ የሚቆጠሩት መፃህፍትን ለትምህርት ቤቶች ማድረሳቸውን የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች ይገልጻሉ።

ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል

ቴክኖሎጂ ያመጣለትን ዕድል ተጠቅሞ የወጣቶች የማንበብ ባህልን ለማሳደግ እየሰራ የሚገኘው ወጣት ይርጋ ገብረመድህን፤ መፃሕፍት ሰብስበህ መሄድ በቻ በቂ ስላልሆነ ሕብረተሰቡ የማንበብ ባህል ጠቀሜታ እንዲረዳ የሚያግዙ ሲምፖዝየሞች ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው ይላል።

ባለፈው ዓመት ከአንድ ሺ መፃሕፍት በላይ አሰባስቦ ወደ ሽረ እንዳሥላሴ ከተማ ማቅናቱን የሚናረው ወጣት ይርጋ ከአክሱም ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ከስድስት መቶ በላይ ጎበዝ ተማሪዎች የተሳተፉበት ሲምፖዝየም መዘጋጀቱን ይገልጻል።

መኖርያው አሜሪካ ያደረገው እና በመፃሕፍት ልገሳ ላይ የሚሳተፈው አቶ ጸጉ ብርሃነ የእስራኤል ተሞክሮ በማንሳት ኢትዮጵያም እንዲሁ ማደግ እምትችለው አንባቢ ማሕበረሰብ ስትፈጥር ነው ይላል።

ሕዳር ጽዮን እና ንባብ

በየዓመቱ በአክሱም ከተማ በሚከበረው ሀይማኖታዊ ክብረ በዓል 'ሕዳር ጽዮን' እስከ ግማሽ ሚልዮን የሚጠጋ እንግዳ እንደሚሳተፍበት የትግራይ ክልል የባህል እና ቱሪዝም መረጃ ያመላክታል።

ታዲያ ከዚህ ሀይማኖታዊ ክበረ በዓል ጎን ለጎን ሕብረተሰቡ የማንበብ ባህሉን የሚያሳድግበት ሲምፖዝም መካሄዱን ከመድረኩ አስተባባሪዎች ይናገራሉ።

ተያያዥ ርዕሶች