ሰሜን ኮሪያን ለዚህ ያበቃቻት አሜሪካ ናት ስትል ሩሲያ ወቀሰች

የሰሜን ኮሪያ ሚሳኤል ርቀት

የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ አሜሪካ ሰሜን ኮሪያን በመነካካት የኑክሌር ሚሳኤል ፕሮግራሟን አጠናክራ እንድትገፋበት አድርጋለች ሲሉ ከሰሱ።

በተጨማሪም ሰሜን ኮሪያ ያደረገችውን ተጨማሪ የተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራን ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የአሜሪካ መልዕክተኛ፤ ሃገራት ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ ያቀረቡትን ጥሪ ውድቅ አድርገውታል።

ሩሲያ ማዕቀብ መፍትሄ ስለማያመጣ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ድርድር እንዲካሄድ ጥሪ እያደረገች ነው።

የአሜሪካ ጦርነት ከተቀሰቀሰ የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ''በማያዳግም ሁኔታ ይደመሰሳል'' በማለት አስጠንቅቃለች።

በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ረቡዕ ዕለት ያደረገቸውን የሚሳኤል ሙከራ ተከትሎ፤ አህጉረ አሜሪካን በሚሳኤሎቿ የመምታት ርቀት ውስጥ መሆኑን ሰሜን ኮሪያ ገልፃለች።

ቢሆንም ግን የመከላከያ ባለሙያዎች የኑክሌር አረር ተሸክመው ረጅም ርቀት ለመጓዝ የሚያስችለው ብቁ ቴክሎሎጂ ላይኖራት ይችላል በሚል በሚሳኤሎቹ የመምታት ርቀት ላይ ጥርጣሬ አላቸው።

Image copyright AFP