በኢትዮጵያ ስላሉ ስደተኞች አንዳንድ ነጥቦች

በኢትዮጵያ ያሉ ስደተኞች Image copyright Getty Images

በኢትዮጵያ ውስጥ ከ847 ሺህ በላይ ስደተኞች አሉ። ይህ ቁጥርም ስደተኞችን በመቀበል ሃገሪቱን በአፍሪካ ሁለተኛ እንደሚያደርጋት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ ያሳያል።

እነዚህ ስደተኞች አብዛኛውን ጊዜ ግጭትና አለመረጋጋት ካለባቸው እንደ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራና ሱዳን ካሉ ሃገራት ቢመጡም በአጠቃላይ የ19 ሃገራት ዜግነት ያላቸው ስደተኞች ናቸው።

ስደተኞቹ በአብዛኛው በትግራይ ክልል መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በሶማሌ ክልሎች ተጠልለው ይገኛሉ።

ስደተኝነት እንዴት ተቀባይነት ያገኛል?

ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ መንግሥት ከለላ ለሚፈልጉ ስደተኞች በሩ ክፍት እንደሆነ ነው። ይህንንም ለማድረግ ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ፈርማለች።

ብዙዎቹ ስደተኞች ያለውጣ ውረድ ወዲያው የጥገኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያገኛል። የእያንዳንዱም ስደተኞች ጉዳይ የሚወሰነው በኢትዮጵያ መንግሥት በተዋቀረ ኮሚቴ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽንም በታዛቢነት ጉዳዩን ይከታተላል።

ሃገሪቱ በስደተኝነት የተቀበለቻቸውንም ሆነ ጥገኝነት ጠያቂዎች መንግሥት በመደባቸው የመጠለያ ጣቢያዎች መቀመጥ የሚኖርባቸው ሲሆን፤ ቁጥራቸው ብዙ ባይሆንም በከተማ ውስጥ እንዲኖሩ ፍቃድ ያላቸውም አሉ።

እነዚህም ከህክምና፣ ከደህንንት እንዲሁም ከሌሎች ችግሮች ጋር በተያያዘ ምክንያት መጠለያ ውስጥ መቆየት የማይችሉ ናቸው።

በአዲስ አበባ ውስጥ 17345 ስደተኞች አሉ። ይህ የመንግሥት "ከመጠለያ ጣቢያ ውጭ" ከሚለው ፖሊሲ በተጨማሪ ኤርትራውያን ስደተኞች በአዲስ አበባም ይሁን በሌሎች ከተሞች ራሳቸውን ማስተዳደር ከቻሉ መኖር የሚችሉበት መንገድ ተመቻችቶላቸዋል።

ህጻናት ስደተኞች

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ847 ሺህ በላይ ስደተኞች አሉ

መንግሥት ከመጠለያ በተጨማሪ አትኩሮት የሚሰጥባቸው ጉዳዮች አሉ። እነዚህም ለህፃናት ስደተኞች ጥበቃ፣ ትምህርት፣ ወሲባዊም ሆኑ ፆታዊ ጥቃቶችን መከላከል ናቸው።

በተለይም ከኤርትራ ከቤተሰብ እገዛ ውጭ ብቻቸውን የመጡ ህፃናት በሽረ አካባቢ ለመንግሥትም ሆነ ለተለያዩ መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች አሳሳቢ እንደሆኑ እየተገለፀ ነው።

የእርሻ መሬት መስጠት

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የ19 ሃገራት ዜግነት ያላቸው ስደተኞች በኢትዮጵያ ይገኛሉ

የስደተኞች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ ሲሆን በተለይም ከደቡብ ሱዳን ጦርነት ጋር ተያይዞ 200 ሺህ የሚገመቱ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።

በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ የስደተኞችን ህይወት ለማሻሻል የተለያዩ ፕሮጀክቶችም እየተቀረፁ ነው።

ከእነዚህም መካከል ለወደፊት የተያዙት ዕቅዶች ከመጠለያ ውጭ ያሉ ቦታዎችን ማስፋፋትና ቢያንስ 10% ስደተኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ፤ ለስደተኞች የሥራ ፈቃድ መስጠት፤ የስደተኛ ልጆችን በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች እንዲሳተፉ ማድረግ፤ 10 ሺህ ሄክታር የሚታረስ መሬት 20ሺ ለሚሆኑ ስደተኞች መስጠትና የራሳቸውን እርሻ የሚያለሙበትን መንገድ መፈለግ እንዲሁም ከኢትዮጵያውያን ጋር በቀላሉ እንዲዋሃዱ የማስተሳሰር ፕሮግራም ይገኙባቸዋል።