ምድብ አራት፡ አርጀንቲና፣ አይስላንድ፣ ክሮሺያ እና ናይጄሪያ

John Mikel Obi Image copyright AFP

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ተጠናቆ አዘጋጇ ሩሲያን ጨምሮ ወደ ዓለም ዋንጫው ያለፉ 32 ሃገራት ተለይተዋል።

የአምስት ጊዜ አሸናፊዋ ብራዚልን ጨምሮ ያለፈው ጊዜ አሸናፊዋ ጀርመን፣ ሩሲያ፣ አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ፣ ቤልጂም፣ ኮሎምቢያ፣ ኮስታሪካ፣ ክሮሺያ፣ ዴንማርክ፣ ግብጽ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ አይስላንድ፣ ኢራን፣ ጃፓን፣ ሜክሲኮ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ፓናማ፣ ፔሩ፣ ፖላንድ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሴኔጋል፣ ሰርቢያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ስፔን፣ ስዊዲን፣ ስዊዘርላንድ፣ ቱኒዝያ እና ኡራጋይ ናቸው በ2018ቱ ዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉት።

እነዚህ ሃገራት እንዴት እዚህ ደረሱ? ለውድድሩ ያበቋቸው ኮከብ ተጫዋቾች እነማን ናቸው? ለውድድሩ ያበቋቸው አሰልጣኞችስ እነማን ናችው?

እያንዳንዱን ሃገር በምድብ ከፋፍለን እንመለከታለን።

ምድብ አራት

Image copyright AFP

አርጀንቲና

የቀደመ ታሪክ፡ አርጀንቲና የዓለም ዋንጫን ሁለት ጊዜ በ1978 እና በ1986 አሸንፋለች። በ1930፣ በ1990 እንዲሁም በ2014 የብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ደግሞ ሁለተኛ በመሆን አጠናቀዋል። ሊዮኔል ሜሲ በ2008 ቤጂንግ ኦሎምፒክ አርጀንቲና የወርቅ ሜዳሊያ እንድታገኝ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።

ቁልፍ ተጫዋቾች፡ ሊዮኔል ሜሲ። ሜሲ ለአምስት ጊዜ ያህል የዓለም ምርጥ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠ ሲሆን አርጀንቲና ከኢኳዶር ጋር ባደረገችው ግጥሚያ ሃትሪክ ሰርቷል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? ቺሊን በ2015 ወደ ኮፓ አሜሪካ የመሩት ጆርጅ ሳምፖሊ በ2017 ግንቦት ወር አርጀንቲና አሰልጣኝ ተደርገው ተመርጠዋል። አርጀንቲና ለዓለም ዋንጫ እንድታልፍ በማድረግ የመጀመሪያ ሃላፊነታቸውንም ተወጥተዋል።

አይስላንድ

የቀደመ ታሪክ፡ ኮሶቮን ካሸነፉ በኋላ አይስላንዶች ወደ ሩሲያ የሚያቀኑት የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ውድድራቸውን ለማድረግ ነው። በዩሮ 2016 ላይ ከተሳተፉ በኋላ የአሁኑ ስኬታቸው ቡድኑ ወርቃማው ትውልዳቸው መሆኑን በትክክል ያረጋገጡበት ነው። በአውሮፓ ዋንጫ ላይ እንግሊዝን በሁለተኛው ዙር ያሸነፉ ሲሆን በሩብ ፍጻሜው በፈረንሳይ 4 ለ 2 ተሸንፈዋል።

ቁልፍ ተጫወዋች፡ ከኤቨርተኑ ግይል ሲጉርድሰን ውጭ ሌላ ተጫዋች መፈለግ ከባድ ነው። የ28 ዓመቱ አማካይ ኮሶቮ ላይ የመጀመሪያዋን ጎል ያስቆጠረ ሲሆን ጎሏም ከርቀት የተቆጠረች ምርጥ ጎል ናት።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? የሃምሳ ዓመቱ የጥርስ ሐኪም ህይሚር ሃልግሪምሰን ቡድኑን በፈረንሳይ የአውሮፓ ዋንጫ ላይ የስውዲኑ አሰልጣኝ ላገርባክ ምክትል በመሆን መርተዋል። ሃልግሪምሰን ከውድድሩ በኋላ ቡድኑን በመረከብ ውጤታማ የሚባል የማጣሪያ ጉዞ አድርገዋል።

Image copyright Rex Features

ክሮሺያ

የቀደመ ታሪክ፡ ክሮሺያ በፊፋ አባልነት የተመዘገበችው እ.አ.አ በ1993 በመሆኑ በቀጣዩ ዓመት ለተዘጋጀው የአሜሪካ ዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ በቂ ጊዜ አልነበራቸውም። ሆኖም ፈረንሳይ ባዘጋጀችው ቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ችላለች። ከዛ በኋላም በአራት ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ለመሆን በቅታለች። በፈረንሳዩ የዓለም ዋንጫም እስከ ግማሽ ፍጻሜ ብትጓዝም በውድድሩ አዘጋጅና አሸናፊ ፈረንሳይ ተሸንፋለች።

ቁልፍ ተጫዋች፡ የሪያል ማድሪዱ ሉካ ሞድሪች ለክሮሺያ ብሄራዊ ቡድን የመሐል ሞተርና ኳስ አቀጣጣይ ነው። የአስደናቂ ዕይታ እና የኳስ ስርጭት ክህሎት ባለቤት የሆነው ተጫዋች ከክለቡ ጋር ሶስት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል። በቅርቡ ለብሔራዊ ቡድኑ 100ኛ ጨዋታ ማድረግ የቻለው ሞድሪች 12 ጎሎችንም ማስቆጠር ችሏል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? አጭር ጊዜ ቢሆንም የክሮሺያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ዝላትኮ ዳሊች ጣፋጭ ጊዜን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር እያሳለፉ ነው። አንቴ ካቺችን በመተካትም ስራውን የጀመሩት ከሁለት ወራት በፊት ሲሆን ሃገሪቱ ለዓለም ዋንጫው የማለፍ ዕጣዋ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ በነበረበት ወቅት ነው። በደርሶ መልስ ጨዋታ ግሪክን 4 ለ 1 በማሸነፍም ነው ወደ ሩሲያ የሚወስዳቸውን ቲኬት መቁረጥ የቻሉት። በተጫዋችነት ዘመናቸው አማካይ የነበሩት ካቺችን ከአስር ዓመታት የአሰልጣኝነት ዘመናቸው ሰባቱን በሳዑዲ አረቢያ እና ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ነው ያሰላፉት።

ናይጄሪያ

የቀደመ ታሪክ፡ ይህ የዓለም ዋንጫ ናይጄሪያ ለ6ኛ ጊዜ የምትሳተፍበት ሲሆን ለሶስት ተከታታይ ጊዜ የውድድሩ ተሳታፊ የሆነችበትም ነው። በ1994፣ በ1998 እና በ2014 16 ውስት መግባት ብትችልም ከዚህ በላይ ግን ተራምዳ አታውቅም።

ቁልፍ ተጫዋች፡ ልቡድኑ 80 ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈው የቡድኑ አምበል ጆን ሚኬል ኦቢ ይጠበቃል። ይህ ለ30 ዓመቱ የቀድሞው የቼልሲ አማካይ ሁለተኛው የዓለም ዋንጫ ሲሆን በ2014 ቡድኑ በ 16 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥሎ ማለፍ ላይ እንዲደርስ አግዟል። በ2013 ሃገሩ የአፍሪካን ዋንጫ እንድታነሳ የድርሻውን ተወጥቷል። አሁን ደግሞ ለቻይናው ቲያንጂን ቴዳ በመጫወት ላይ ይገኛል።

አሰልጣኙ ማን ናቸው? የ64 ዓመቱ ጀርመናዊ ገርኖት ሮር በኒስ፣ ጋቦን፣ ቡርኪናፋሶና ናይጄሪያን ጨምሮ የተለያዩ ቡድኖችን ሲያሰለጥኑ የቆዩ ናቸው። በባየርሙኒክና በቦርዶ ተጫውተዋል። የፈረንሳዩን ናንተስ፣ የስዊዘርላንዱን ያንግ ቦይስ በርኔ ፣የቱኒዚያውን ኢቶይሌ ዱ ሳህልና የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድንን አስልጥነዋል።